ከደረሰኝ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ የ10 ሺህ ብር ጉቦ የተቀበሉ 3 የቁጥጥር ባለሙያዎች እጅ ከፍንጅ መያዛቸው ተገለፀ

AMN – ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የንፋስ ስልክ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅ/ቤት 3 የደረሰኝ ቁጥጥር ባለሙያዎች ከደረሰኝ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ የ10 ሺህ ብር ጉቦ ሲቀበሉ በፖሊስ እጅ ከፍንጅ መያዛቸው ተጠቁሟል፡፡

የፅኅፈጽ ቤቱ የህግ ማስከበር ዘርፍ ም/ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ይታይሽ ቢረሳው ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት የቁጥጥር ባለሙያዎቹ እጅ ከፍን ልያዙ የቻሉት የአዲስ አበባ ቁጥር 2 የገቢዎች ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ግብር ከፋይ የሆነ ግለሰብ ለፖሊስ ባደረሰው ጥቆማ ነው።

ተጠርጣሪዎቹ ድርጊቱን የፈፀሙት አርብ ታህሳስ 11 ቀን 2017ዓ. ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፔፕሲ እየተባለ በሚጠራ አካባቢ ጉልደን የታሸጉ ውሃዎች አምራችና አከፋፋይ ድርጅት ላይ ነው፡፡

ጥቆማው የደረሰው የክፍለ ከተማው ፖሊስ የኢንቨስትጌሽን ስራ በማከናወን ከውሃ አምራችና አከፋፋይ ድርጅቱ ባለቤት ከሆኑ ግለሰብ ጥቆማው እንደደረሰው ወዲያውኑ ባካሄደው የኦፕሬሽን ስራ ተጠርጣሪዎቹ የ10 ሺህ ብር ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ሊያዙ መቻሉንም ተናግረዋል።

እንደ ምክትል ስራ አስኪያጇ ገለፃም ተጠርጣሪዎቹ የቁጥጥር ባለሙያዎቹ ከአንድ ሳምንት በፊት ከዚሁ ድርጅት የሽያጭ ባለሙያ ከደረሰኝ ቁጥጥር ጋር የ20ሺህ ብር ጉቦ መቀበላቸው በመረጃ ተረጋግጧል ብለውናል፡፡

በአሁኑ ወቅት ተጠርጣሪዎቹ በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን የቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ የህግ ዘርፍ ምክትል ስራአስኪያጇ ተናግረዋል፡፡

አክለውም ወንጀሉን ለፖሊስ በማጋለጥ በሌብነት ድርጊት ውስጥ የገቡ የቁጥጥር ባለሙያዎች ጉዳያቸው በህግ እንዲታይና በገቢ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ በኩል አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ላደረጉ የጎልደን የታሸጉ ውሃ አምራችና አከፋፋይ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ባለቤት ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ የቁጥጥር ባለሙያዎችና ሌሎች በገቡት ቃል መሰረት ተግባሮቻቸውን ከሌብነትና ብልሹ አሰራር በፀዳ መልኩ ሊፈፅሙ እንደሚገባ በመጠቆም በአሁኑ ወቅት በሌብነት ድርጊት ተጠርጥረው በህግ ጥላ ስር የሚገኙ የቅንጫፍ ፅ/ቤቱ የቁጥጥር ባለሙያዎችም ሌሎች አስተማሪ የሆነ እርምጃ ይወሳደል የሚል እምነት እንዳላቸው መናገራቸውን ከገቢዎች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review