ከ4ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ንብረቶችን የሰረቁ ተጠርጣሪዎችና ተቀባዮች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

You are currently viewing ከ4ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ንብረቶችን የሰረቁ ተጠርጣሪዎችና ተቀባዮች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

AMN – መስከረም 10 /2017 ዓ.ም

ሁለት ተጠርጣሪዎች መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ/ም ከሌሊቱ 10 ተኩል በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በወረዳ 5 ክልል በመገንባት ላይ በሚገኘው አዳምስ ህንፃ ላይ የተዘረጉ የኤሌትሪክ ገመዶችን ለመስረቅ አጥር ዘለው መግባታቸው ተገልጿል፡፡

በወቅቱ በወንጀል መከላከል ስራ ላይ በነበሩ የፖሊስ አባላት ተይዘው የተፈተሸ ሲሆን የኬብል መቁረጫና ሁለት ቦርሳ እንደተገኘባቸው ተነግሯል።

የተፈፀመውን ወንጀል መነሻ በማድረግ በተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ ማስፋት ስራ መስራቱን ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

በምርመራ ማስፋት ሥራው ግለሰቦቹ በክፍለ ከተማው ወረዳ 1 በፀጋ ሆስፒታል አካባቢ ከሚገኘው አንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት የሰረቁትን ንብረት እንደሚያስረክቡ በመረጋገጡ በህግ አግባብ በተደረገ ብርበራ 50 ጥቅል የኤሌትሪክ ገመዶች ፣ 5ጥቅል የኤል ኢ ዲ ኬብል ፣ ልዩ ልዩ አይነት ሌሎች ኬብሎች እና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን እንዲሁም ከዚህ ቀደም ከአዳምስ ህንፃ የተሰረቁ የኤሌትሪክ ገመዶች መገኘቱን ፖሊስ መምሪያው አስታውቋል።

ከዚህ የወንጀል ድርጊት ጋር በተገናኘም የስርቆት ወንጀል በመፈፀም የተጠረጠሩና የተሰረቀ እቃ የሚገዙ ሁለት ተቀባዮች ተይዘው ምርመራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ጨምሮ ገልጿል።

የአዳምስ ህንፃ ተወካይ ወ/ሮ ቤተልሄም ክፍሌ በበኩላቸው፤ ተመሳሳይ የስርቆት ወንጀል በተቋማቸው ላይ ሲፈፀም መቆየቱን አስተውሰው ፖሊስ ለጉዳዮ ትኩረት በመስጠት ባከናወነው ተግባር ወንጀል ፈፃሚዎቹ ተይዘው የተሰረቀው ንብረት በመገኘቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡

ወንጀል ፈፃሚዎቹ መሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ትኩረት አድርገው ወንጀል ሲፈፅሙ እንደነበር መረጋገጡንና ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ የስርቆት ወንጀል የተፈፀመባቸው ተቋማት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በመቅረብ ንብረታቸውን እንዲለዩ ጥሪ ተላልፏል።

የሌባ ተቀባዮች ላይ እየተወሰደ ያለው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቀው ፖሊስ ህብረተሰቡ ጥቆማና መረጃ በመስጠት እንዲተባበር የአዲስ አበባ ፖሊስ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ጥሪ አስተላልፏል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review