ክፍለጦሩ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን የአሸባሪው ሸኔ ቡድንን መደምሰሱን አስታወቀ

You are currently viewing ክፍለጦሩ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን የአሸባሪው ሸኔ ቡድንን መደምሰሱን አስታወቀ

AMN- ጥቅምት 11/2017 ዓ.ም

የምዕራብ ዕዝ ክፍለጦር በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ሀባቡ ወረዳ ቢቂልቱ እንባቦ በተባለ ቦታ ላይ ከግንደ በረት ተነስቶ ደዱ ከተማ ለመግባትና የለመደውን የውንብድና ተግባር ለመፈፅም ሲሞክር ክፍለጦሩ በወሰደው እርምጃ በርካታ የሽብር ቡድኑ አመራሮችና አባላት ተደምስሰዋል።

የክፍለጦሩ ዋና አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ገዛሃኝ በቀለ ክፍለጦሩ መንግስትና ህዝብ የሰጠውን ተልዕኮ ተቀብሎ በቀጠናው አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ሌት ተቀን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በርካታ ድሎችን እያስመዘገበ መሆኑን ገልፀዋል።

ጠላት ያለ የሌለ ሃይሉን በመጠቀም የለመደውን የሽብር ጥቃት ለማድረስ ቢሞክርም የተመኘውን ከንቱ ምኞት ክፍለ ጦሩ በማምከን የሽብር ቡድኑን ከፍተኛ አመራሮችና አባላትን መደምሰስ መቻሉን ተናግረዋል።

አሁንም ሰላም ጠል የሆነውን አሸባሪውን ቡድን በየገባበት ገብተን የመምታትና የመደምሰስ ተልዕኳችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት አዛዡ በነበረው ስምሪት የተገኘው ከፍተኛ ድል የጠላት ሰብዓዊና ማቴሪያላዊ ኪሳራ መድረሱ የሚያሳየው የሰራዊቱን ቁርጠኝነት ነው ብለዋል።

ምክትል አሥር አለቃ ሳላዲን ሰይድ የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ በሆነ የሰው ሀይል በማጥቃት ወደ ከተማ ለመግባትና ዘርፎ ለመውጣት ቢሞክርም የተስፋ ህልሙን በማጨለም ዳግመኛ እንዳይሞክር ተደርጎ ተመትቷል ብሏል።

አሸባሪው ቡድን ሽብር ለመንዛት አቅዶና ተዘጋጅቶ ቢመጣም ከ16 በላይ የነብስ ወከፍና የቡድን መሳሪያ፣ ወታደራዊ ትጥቆች ፣ በርካታ ተተኳሾችና የእጅ ቦምቦች እንዲሁም 3 ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ሰራዊቱ ባደረገው ተጋድሎ መማረኩን ከሀገር መከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review