የሎስ አንጀለስ ሰደድ እሳት መንሥኤው ምንድን ነው?

You are currently viewing የሎስ አንጀለስ ሰደድ እሳት መንሥኤው ምንድን ነው?

AMN – ጥር 6/2017 ዓ.ም

በርካቶችን ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀለው እና ለኅልፈትም የዳረገው የሎስ አንጀለሱ ሰደድ እሳት በምን ምክንያት እንደተቀሰቀሰ በመንግሥት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

በዋናነት ፓሊሴድ እና ኢቶን የተሰኙ እሳቶች ከተማዋን ወደ አመድነት ቀይረዋታል።

የሎስ አንጀለስ አስተዳደር በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛ ጉዳት በማስከተል አቻ ያልተገኘለት የግዙፉን ሰደድ እሳት መንሥኤ እያስጠናሁ ነው ብሏል።

ጥናቱ ይፋ ባይሆንም የዘርፉ ባለሙያዎች ለአደጋው መንሥኤ ይሆናሉ ያሏቸውን ነጥቦች ከማብራራት እንዳልቦዘኑ ቢቢሲ በዘገባው አስነቧቧል።

በካሊፎኒያ የፈረንጆቹ 2022 እና 2023 እጅግ እርጥበታማ ዓመታት ነበሩ።

በነዚህ ዓመታት በልምላሜ የተሞላው ምድር ረጃጅም ተክሎችንም ያበቀለበት ወቅት ነበር።

ይሁናን በተጠናቀቀው 2024 ላይ የተከሰተው ደረቃማ አየር ተክሎቹን በማድረቁ ለሰደድ እሳቱ በመንሥኤነት ይጠቅሳሉ የዘርፉ ባለሙያዎች።

ሎስ አንጀለስ ከጥቅምት ወዲህ 0 ነጥብ 16 ኢንች ዝናብ ብቻ ነው ያገኘችው።

ደረቃማው አየር እና ከውቅያኖስ ዳርቻዎች የሚነሣው ‘ሳንታ አና’ የተሰኘው ከባድ ንፋስ ተዳምረው ለሰደድ እሳቱ መፈጠር ምክንያት ሳይሆኑ እንዳልቀረም ነው ባለሞያዎቹ ያከሉት።

የአየር ንብረት ለውጥም በእሳት አደጋው የራሱ አስተዋፆ እንዳለው ይገለጻል።

በተለይም በአውስትራሊያ እና በምዕራብ አሜሪካ ከሁለት ዓመታት በፊት ለ10 ዓመታት የተስተዋለው የዝናብ እጥረት፣ ከባድ እና ደረቅ አየር አካባቢውን ተጋላጭ አድርጓል ይላሉ ባለሙያዎቹ።

የሰደድ እሳቱን ሰበቦች አስመልክቶ በዘርፉ ባለሙያዎች የሚሰጠው መላ ምት እንዳለ ሆኖ በነዋሪዎች በኩል ያለው ደግሞ ሌላ ነው። ነዋሪዎቹ ችግሩ ከኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ያነሣሉ።

ከፈረንጆ 1992 ወዲህ ከተከሰቱት የሰደድ እሳት አጋጣሚዎች መካከል ከ3 ሺህ 600 በላይ የሚሆነው በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች፣ ማስተላለፊያዎች እና ማከፋፈዎች ጋር የተያያዘ መሆኑን የአሜሪካ የደን አገልግሎት መረጃን ጠቅሶ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

በ2017 የተቀሰቀሰው እና ለ40 ቀናት የነደደው ‘ቶማስ’ የተባለው እሳት የተፈጠረው በንፋስ ግፊት ምክንያት የኤሌክትሪክ መስመር ተጠላልፎ በተፈጠረ እሳት መሬት ላይ ከሚገኙ እና ወዲያው ሊቀጣጠሉ ከሚችሉ የደረቁ ተክሎች ጋር ተገናኝቶ በስፋት ሊዛመት ችሏል።

በተመሳሳይ መልኩ በተለያዩ ዓመታት ከኤሌክትሪክ ጋር የተያያዙ የእሳት አደጋዎች በካሊፎኒያ ያጋጠሙ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ሆን ተብሎ በሰዎች የሚደረግ የቃጠሎ ወንጀል እና የመብረቅ አደጋዎች ለመሰል የሰደድ ችግሮች በመንሥኤነት ይነሣል።

ምንም እንኳ እስካሁን ድረስ በመንግሥት በኩል የተገለጸ ነገር ባይኖርም በደቡብ ካሊፎርኒያ አካባቢ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው ‘ኢቶን’ የተሰኘው ሰደድ እሳት ከኤሌክትሪክ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የተፈጠረ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ከፈረንጆቹ 1800 ጀምሮ በካሊፎርኒያ ከ12 ሺህ 500 በላይ ሰደድ እሳት ተከስቷል።

ከነዚህም መካከል ግማሽ ያህል የሰደድ እሳቱ መንሥኤ ምን እንደሆነ አለመታወቁ ተገጿል።

በሎስ አንጀለሱ ሰደድ እሳት እስካአሁን 24 ሰዎች ሞተዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ወደ አመድነት ተቀይረዋ፤ ከ100 ሺህ የሚልቁትን ደግሞ ከመኖሪያቸው አፈናቅሎ ዛሬም ሳይገታ ጉዳት ማድረሱን ቀጥሏል።

ምንሥኤው ምን ይሆን የሚለው ግን እስካሁን አልታወቀም

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review