AMN – ጥቅምት 15/ 2017 ዓ.ም
የሕንፃ ሥር የተሽከርካሪ ማቆሚያ ስፍራዎችን ለሌላ አገልግሎት ባዋሉት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ገልጿል።
ባለስልጣኑ የተሸከርካሪ ማቆሚያ ስፍራዎችን ማስተዳደር የሚያስችለውን ደንብ ቁጥር 165/2016 ከተማ አስተዳደሩ ማጽደቁ ይታወሳል።
ደንቡ ለዚሁ አገልግሎት የተገነቡ ህንጻዎች፣ ስፍራዎችና በግል ህንፃ የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት የሚሰጡትንም ያካትታል።
በከተማው ህግን በመጣስ አብዛኞቹ የህንጻ ባለንብረቶች ለመኪና ማቆሚያነት ፈቃድ ያገኙበትን ቦታ ሸንሽነው ለንግድና ለሌሎች አገልግሎቶች ማዋላቸውን ጥናቶች ያመላክታሉ።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማረ ታረቀኝ እንደገለጹት በከተማው በህንጻዎች ስር የተገነቡ የመኪና መቆሚያ ስፍራዎች አብዛኞቹ ለታለመላቸው ዓላማ እየዋሉ አለመሆኑ ተናግረዋል።
ችግሩን ለመፍታት የህንጻ ባለንብረቶች፣ በዘርፉ ተሰማርተው የመኪና ማቆሚያ ያላቸውን ሰዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ የማስጨበጥና ችግሩ እንዲቃለል ሰፊ ስራ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።
ነገር ግን ችግሩ በግንዛቤ ማስጨበጥ ብቻ የሚመለስ ባለመሆኑ ተቋሙ በቅርቡ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የትራፊክ ፍሰቱ እንዲሳለጥ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የትራፊክ አደጋ በሰው ህይወት ላይ እያሳደረ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ለችግሩ መንስኤ የሆኑ ነገሮችን በመለየት መፍትሄ እንዲያገኙ ተቋሙ እየሰራ መሆኑን አክለዋል።
ለአብነትም የትራፊክ አደጋን መከላከል በሚያስችሉ አጀንዳዎች ላይ ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን የመስጠትና ሌሎች ተግባራተን እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
በከተማዋ የትራፊክ አደጋን መከላከል ከሚያስችሉ ተግባራት መካከል የትራፊክ ፍሰቱን የተሳለጠ እንዲሆን ማስቻል መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ይህም እውን እንዲሆን በመንግሥት በኩል በከተማዋ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎችን ታሳቢ ያደረጉ በመሆናቸው የትራንስፖርት እንቅስቃሴው ቀልጣፋ እንዲሆን አቅም እየፈጠረ ነው ብለዋል።