ወንዞች ንጹህ ሆነው ታዩ፡፡ ጋራ ሸንተረሩ አደይ አበባ ለበሰ፡፡ ምክንያቱም መስከረም ገብቷል። ወርሃ መስከረም ከገባ ቀናት መቆጠር ጀምረዋል። የዘመን መለወጫ በዓል ስሜቱና ድባቡ ግን እንደቀጠለ ነው፡፡ ከመልክዐ ምድሩ ውበት በተጨማሪ ውብ እና ድንቅ የሆኑ በዓላት የሚከበሩበት ወርም ነው፡፡ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም በወሩ ውስጥ ስለሚከበሩ በዓላት በጥቂቱ እንደሚከተለው አዘጋጅቷል፡፡
የዘመን መለወጫ በዓል
ተናፋቂው መስከረም በዘመን መለወጫ በዓል አንድ ብሎ ይጀምራል፡፡ በዓሉም በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ በጉጉት የሚናፈቅና በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ነው፡፡ የኢትዮጵያ የወራት ሁሉ መጀመሪያ መስከረም ነው፡፡ መስከረም ወር ዘመን መለወጫ፣ ዕንቁጣጣሽ በሚሉ እና በሌሎች ስሞች ይጠራል፡፡
አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት፣ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር የዕድሜያችን ቁጥር የሚጨምርበት ብቻ ሳይሆን በኑሮ ላይም አዎንታዊ ለውጥን ለማድረግ ዕቅድ ይዘን የምንነሳበትም ነው። አዝመራዉ እንዲያሽት፣ ውጥን እንዲሳካ፣ የጠባው አዲስ ዓመትም ሰላምን፣ ጤናን፣ ፍቅርንና መግባባትን ሰንቆ እንዲያልፍ ምኞት የሚገለጽበት ጭምር ነው። በአዲስ ዘመን ሀገርና ህዝብ በአዲስ መንፈስ፣ በአዲስ ዕቅድና በአዲስ ተስፋ መጪውን ዘመን ይቀበሉታል፤ ከአሮጌው ዘመን በመማር ለአዲሱ ዓመት የተለያዩ ዕቅዶችን ያወጣሉ ይላል ዶቼቬለ እ.ኤ.አ በ2010 በአዲስ ዓመት “አዲስ ግብ አዲስ ተስፋ” በሚል ርእስ ባሰፈረው ጹሑፍ። በእርግጥም መስከረም አዲስ ነው፡፡ ተማሪዎች በአዲስ መንፈስ ወደ ትምህርት ቤት ያቀናሉ፡፡ ሰዎች በአዲስ ስሜት ለአዲስ ለውጥ ይነሳሉ። ሁሉም አዲስ ነው፡፡ የዘመን መለወጫም በመስከረም ወር የሚከበረው የመጀመሪያው በዓል ነው፡፡
መውሊድ
መውሊድ ነቢዩ ሙሐመድ የተወለዱበት ቀን ሲሆን ይህንኑ የእስልምና እምነት ተከታዮች ያከብሩታል። የመውሊድ በዓል በተለያዩ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ማለትም በጸሎት፣ የነቢዩን የሕይወት ተሞክሮ በመተረክ፣ ስብእናቸውን በማወደስ (በመንዙማና ነሺዳ)፣ በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በመሳተፍና ልዩ ልዩ ልመናዎችን (ዱዓ ወይንም ጸሎት) በማቅረብ ይከበራል፡፡
የፎክሎር ባለሙያው መሐመድ ዓሊ (ዶ/ር) እንደሚሉት በኢትዮጵያ መውሊድ መከበር የጀመረው በአሥራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ እንደሆነ ይታመናል። ብሄራዊ ክብረ በዓል የሆነውም በደርግ ዘመን ከ1967 ዓ.ም ወዲህ ነው፡፡
መውሊድ ማህበራዊ ፋይዳው የገዘፈ እንደሆነ የፎክሎር ባለሙያው ጉዳዩን አስመልክተው በሰሩት ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ አስፍረዋል፡፡ አንዳንድ ሰዎች መውሊድን ሲያከብሩ ሰደቃ (ደግሶ ደሀን የማብላት ሥርዓት) ያደርጋሉ፡፡ በርካታ ሰዎች ከተለያየ ቦታ ተሰባስበው አብረው በመብላትና በመጠጣት ነብዩ ሙሐመድን በጋራ ያሞግሳሉ። በዚህ ምክንያት ሀብታምና ድሃ ይገናኙበታል፡፡ በቦታ ርቀት ሳቢያ የተጠፋፉና የተነፋፈቁ ሰዎችም ይገናኛሉ፡፡
የፈጣሪ መልእክተኛ የሆኑት ነብዩ ሙሐመድ የታላቅ ስብዕና ባለቤት ሲሆኑ ከሃይማኖታዊ ትምህርት ባሻገር ለማህበረሰቡ የእርስ በእርስ መስተጋብር ጠቃሚ የሆኑ በርካታ ትምህርቶችን በንድፈ ሃሳብና በተግባር ኖረው በማሳየት ሲያስተምሩ ቆይተዋል። ከነዚህም ውስጥ ስለሰዎች እኩልነትና ክብር፣ የጉርብትናን ሃቅ፣ እዝነት፣ መረዳዳትና መከባበር፣ ፍትሃዊነትን እንዲሁም የሰላምን አስፈላጊነት የተመለከቱ ለማህበራዊ ህይወትም ሆነ ለሃገር ሰላም የሚጠቅሙትን ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም የመውሊድ በዓል ሲከበር እነዚህን ጠቃሚ የሆኑ የነብዩን ትምህርቶች በማስተጋባት እንዲሁም እሳቸውን በማወደስና በማውሳት ሊሆን እንደሚገባ የሃይማኖቱ ምሁራን ያስተምራሉ፡፡
መስቀል
በመስከረም ወር ከሚከበሩ በዓላት መካከል መስቀል ሌላኛው ተጠቃሽ ነው፡፡ የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ከሚከበሩ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ይዘት ካላቸው በዓላት ተርታ የሚመደብ ነው። የመስቀል በዓል በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት የሚከበር ሲሆን፤ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶችም በብዛት ይታደሙበታል፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ዘንድ ዕለቱ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ሥነ ስርዓቶች ጭምር ደምቆ ይውላል፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል ማራኪ ህብረ ቀለም ይታይበታል፤ በዝማሬ፣ ችቦና ደመራ በማብራትም ይከበራል፡፡ መስቀል ምንም እንኳን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የራሱ የሆነ ትርጉም ያለው ቢሆንም ከኃይማኖታዊ ክንዋኔው ባሻገር፣ ባህላዊ በሆነ ገፅታ የሚያከብሩት የማህበረሰብ ክፍሎችም በርካታ ናቸው፡፡
የመስቀል በዓል አከባበር በ2006 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የትምህርትና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) መመዝገቡ ይታወሳል፡፡ በዓሉ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ በተካሄደ 8ኛው ጉባዔ ላይ ነበር፡፡
ኢሬቻ
ኢሬቻ በኦሮሞ ማህበረሰብ በወርሃ መስከረም በደማቁ የሚከበር በዓል ነው፡፡ አከባበሩም ከጭጋጋማው ወደ ብርሃናማው ወቅት በሰላም መሸጋገሩን ምክንያት በማድረግ ለፈጣሪ ምስጋና ለማቅረብ እርጥብ ሳር በመያዝ ወደ መልካ (ወንዝ) በመውረድ የሚደረግ ሥነ ስርዓት ነው። የኢሬቻ በዓል ማህበረሰቡ ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት ሥነ ስርዓት ነው፡፡
ኢሬቻ ለበርካታ ወጣቶች እንደ መገናኛ ወይንም ትውውቅ ለመፍጠርም ትልቅ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው፡፡ ይህ የአደባባይ በዓል በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ እንዲሁም በማግስቱ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ተብሎ ይከበራል፡፡
ይህ ክብረ- በዓል በሐይቆች ወይም በወንዞች ዳር የሚከበር ነው፡፡ አደይ አበባና ለምለም ሳር ተይዞ የሚከበር ነው፡፡ በዚህም ከከባዱ የክረምት ወራት በሰላም መሸጋገር፣ ዘመድ አዝማድም መገናኘት በመቻላቸው፣ ክረምት የዘሩትን የእህል ቡቃያ በማየታቸው ፈጣሪያቸውን “ዋቃ”ን ያመሰግናሉ፡፡ መጪው ጊዜም የሰላምና የጤና እንዲሆንላቸውና የበቀለው ቡቃያ ፍሬ እንዲያፈራ ይለምኑበታል፡፡ የመስከረም ወር ድምቀት ከሆኑ በዓላት መካከል የሚጠቀሰው ኢሬቻ ሀገራዊ ይዘታቸውን የጠበቁ ዘመናዊ አልባሳት የሚታዩበት አጋጣሚም ነው። በአጠቃላይ የመስከረም ወር ከተፈጥሯዊ ውበቱ ባለፈ የተለያየ አከባበር ባላቸው በዓላትም የሚደምቅ ወር ነው፡፡
በጊዜው አማረ