AMN – ታኀሣሥ 19/2017 ዓ.ም
የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል በመዲናዋ የተገነቡ የልማት ስራዎችን በጎበኙበት ወቅት፣ የተመለከቷቸው የልማት እንቅስቃሴዎች አዲስ አበባን አዲስ ምዕራፍ ላይ የሚያስቀምጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ልማቶቹ የተቀናጁ፣ በከፍተኛ ጥራት እና ፍጥነት በአጭር ጊዜ የተገነቡ መሆናቸውን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም አዳዲስ የስራ ዕድል የፈጠሩ ናቸውም ብለዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የተሰሩት ልማቶች አንድ ከተማ የመመስረት ያህል ሁሉንም አገልግሎቶች አስተሳስረው የያዙ መሆናቸውንም ሚኒስትሯ አንስተዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ የብልጽግና ፓርቲን እሳቤ የሚያሳዩ ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ ይህም የሰው ልጆችን ጥልቅና ውስብስብ ፍላጎቶች ከግምት ያስገባ ነው ብለዋል፡፡
የተሰሩ የኮሪደርና የአረንጓዴ ልማት ስራዎች የሰው ልጆችን መሰረታዊ ፍላጎቶች ከግምት ያስገቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የኮሪደር ልማት ስራ ባላቸው እና በሌላቸው ዜጎች መካከል ያሉ ልዩነቶችን ማጥበብያ እና ፍትኃዊነትን ማረጋገጫ መንገድ ነውም ብለዋል፡፡
ልማቱ የዜጎችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ያረጋገጠ እንዲሆን ተደርጎ የተቀረጸ መሆኑንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡