የመዲናዋ ፍካቶች

አዲስ አበባ “እንደ ስሜ ልዋብ፣ ገጽታየም ይድመቅ፣ ነዋሪዎችም ሆነ እንግዶች በአግራሞት አፋቸውን ከፍተው ይዩኝ” የሚል ቁጭት ውስጥ ገብታ በጊዜ የለኝም መንፈስ እየሰራች ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ አስረጅ ከተፈለገ ደግሞ በግንባታ በኩል ያለውን ክንውን መምዘዝ ይቻላል፡፡ በ2016 ዓ.ም ግንባታቸው ተጠናቅቆ ወደ አገልግሎት የገቡት ፕሮጀክቶች ከላይ ያለውን ሀሳብ ስጋና ደም የለበሰ ያደርጉታል፡፡ ለዚህ ማሳያዎችን እናንሳ፡-

የከተማዋን  ገፅ  በብዙ  የቀየረው  ልማት

በአዲስ አበባ በ2016 ዓ.ም ግንባታቸው ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ፕሮጀክቶች መካከል የኮሪደር ልማት አንዱ ነው

የኮሪደር ልማት ስራዎች አስረጂ ሳያስፈልግ አፍ አውጥተው የሚናገሩ ውጤቶች ታይተውበታል፡፡ ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ፣ በቀበና፣ እንግሊዝ ኤምባሲ እስከ መገናኛ፤ ከሜክሲኮ እስከ ሳር ቤት፣ ከመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ፣ ከመገናኛ እስከ ሲኤምሲ የተጠናቀቁና ለህዝብ አገልግሎት ክፍት የሆኑ ስራዎች ድንቅ ናቸው፡፡

ደረጃውን የጠበቀ አስፋልት፣ የእግረኛ መንገድ፣ የባለ ሁለት እግር ተሽከርካሪ (ሳይክል) መጠቀሚያ መንገድ፣ ውብ የመንገድ መብራቶች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች፣ ለእይታ ማራኪ የሆኑ አበቦችና የአረንጓዴ ልማት፣ የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች እና የህፃናት መጫወቻ ስፍራ፣ ፋውንቴን፣ ውብ ህንፃ እንዲሁም የደህንነት ካሜራዎች  ልማቱ ካካተታቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመገናኛ እስከ ሲኤምሲ የተጠናቀቀውን ኮሪደር ልማት ለአገልግሎት ክፍት ሲያደርጉ ባደረጉት ንግግር፤ “አዲስ አበባ በቅርብ ዓመታት በኮሪደር ልማቱ ውብ፣ ለመኖር የምትመች፣ የምታጓጓ ከተማ ትሆናለች፡፡ አዲስ አበባን ውብ ካደረግን ከአምስት ዓመት በኋላ ብዙዎች ሊመጡባት የምታጓጓ ከተማ ትሆናለች። የጀመርነውን የኮሪደር ልማት ስራ እንድንጨርስ ሁሉም በጋራ እንዲቆም አደራ” ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ “የኮሪደር ልማት ስራችን ስኬታማ በሆነ ሁኔታ፣ በአጭር ጊዜ፣ እጅግ በጣም ሰፊ አገልግሎቶችን አካትቶ እየተሰራ ነው፡፡ አዲስ አበባ ደረጃዋን የጠበቀች፣ ለህዝባችን ለኑሮ ምቹ ከተማ እናደርጋታለን ላልነው ምስክር የሆነና ውጤታማ ስራ በኮሪደር ልማቱ ተሰርቷል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ ደረጃዋን የጠበቀችና ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን በ2016 ዓ.ም የተጀመረው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ሰፊ እድል ይዞ መጥቷል፡፡ ቀድሞ የነበራት ገፅታ ቀስ በቀስ እየተቀየረ፣ አዲስ፣ ፅዱ፣ ውብ፣ ማራኪና ለነዋሪዎቿ ምቹ እንዲሁም ለቱሪስት መስህብ እንድትሆን እያደረጋት ይገኛል፡፡ በኮሪደር ልማቱ በተሰራው ስራ በሌሎች የውጭ ሃገራት የምናያቸው መሰረተ ልማቶች ዛሬ ላይ በአፍሪካዋ መዲና አዲስ አበባ እየታዩና ውበቷ እየተገለጠ መጥቷል፡፡ ነዋሪውም ከቱሩፋቱ ተጠቃሚ እየሆነ ነው፡፡

በሁለተኛው ምዕራፍም ከየረር እስከ ኮዬ አደባባይ፣ ከቦሌ ሆምስ ወይም ቦሌ አየር መንገድ አዲሱ ተርሚናል፣ ከቦሌ ሚካኤል እስከ ቡልቡላ አደባባይ፣ ከቡልቡላ አደባባይ እስከ ኮየ አደባባይ የኮሪደር ልማት ስራው እንደሚከናወን ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዓመቱ ማጠናቀቂያ የተሰሩ ስራዎችን ሪፖርት ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት አብራርተዋል፡፡

የጥቁሮችን  ታሪክ  የሚዘክረው  መታሰቢያ

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ከፊል ገፅታ

በ2016 በጀት ዓመት ግንባታው ተጠናቅቆ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ሌላኛው ፕሮጀክት  በመሀል አዲስ አበባ ፒያሣ የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ነው፡፡ ዓድዋ በኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይሆን በአፍሪካውያን፣ በዓለም ጥቁርና ጭቁን ህዝብ ልብ ውስጥ የሰረፀ ዘመን አይሽሬ ድል ነው፡፡ ይህ ድል ደማቅና ታላቅ ቢሆንም በሚመጥነው ልክ መዘከሪያ ሳይገነባለት እንደቆየ ይታወቃል፡፡ ከ128 ዓመት በኋላ ድሉን ለመዘከር ግዙፍ የሆነ መታሰቢያ ተገንብቶ በተያዘው ዓመት ለአገልግሎት በቅቷል፡፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያ የተገነባበት ስፍራ ቀድሞ ቆሻሻ መጣያና መፀዳጃ የነበረ ሲሆን፤ መሸት ሲልም ዝርፊያ ይካሄድበት ነበር። መታሰቢያው መገንባቱ ለፒያሣና አካባቢው ግርማ ሞገስንና ውበትን ያላበሰ፣ ቀድሞ የነበረውን ገፅታ የቀየረና ለመዲናዋ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራ እንዲፈጠር ያደረገ ነው፡፡ መታሰቢያው የዓድዋን ድልና ጀግኖቹን የምንዘክርበት ብቻ ሳይሆን ሲገነባና ከተጠናቀቀ በኋላም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድልንም የፈጠረ ፕሮጀክት ነው። ታሪክን የምናውቅበት፣ ከመዝናኛነት ባለፈ የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚከናወንበት መሆኑ ደግሞ ሌላው ተጠቃሽ ድርብርብ ጥቅሞቹ ናቸው፡፡

ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ ፕሮጀክቶች

በአቃቂ ቃሊቲ የተገነባው የ“ለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል”

የጉለሌ የተቀናጀ ልማት ፕሮጀክት ሌላው በ2016 በጀት ዓመት ግንባታው ተጠናቅቆ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከአካባቢው ነዋሪዎች ባለፈ በተለይ እንጨት ከጫካ ለቅመው በመሸጥ ይተዳደሩ የነበሩ እናቶችን ተጠቃሚ ያደረገ እና የሥራ እድልን የፈጠረ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ የጉለሌ የእንጀራ ማእከል፣ የጉለሌ የወተት ማእከል፣ የጉለሌ የመኖሪያ መንደር፣ የምገባ ማእከልና ዘመናዊ መንገድን ያካተተ ነው።

ማእከሉ በከተማዋ ከለሚ የእንጀራ ፋብሪካ ቀጥሎ ሁለተኛው ሲሆን፤ ከ500 በላይ ለሚሆኑ እናቶች በእንጀራ ፋብሪካው የሥራ እድል የፈጠረ ነው፡፡ በጉለሌ የመኖሪያ መንደር በውስጡ 200 አባወራዎችን የሚይዙ ባለ አምስት ወለል አምስት ህንፃዎች ይገኛሉ፡፡ የጉለሌ የወተት ማእከል ደግሞ የወተት ላሞች ሼድ፣ የመኖ ማከማቻ መጋዘን፣ የጥጃ ቤትና የሰራተኞች ማረፊያን ያካተተ ሲሆን፤ በወተት ላም እርባታ የተደራጁ የአካባቢው ህብረተሰብ እየሰሩበት ይገኛል፡፡

የጉለሌ የተቀናጀ ልማት ፕሮጀክትን መርቀው የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በወቅቱ እንዳሉት “ቃል እንገባለን፡፡ ቃላችን በተግባር ነው፡፡ ቃላችንን በተግባር ለመፈፀም የምንሰስተው ጊዜ የለም። ጊዜአችንን፣ ጉልበታችንን፣ ያለንን ሁሉ ለህዝባችን በገባነው ቃል መሰረት ሰርተን እነሆ በተግባር ለማለት ወደ ኋላ እንዳላልን የተሰሩት ስራዎች ህያው ምስክር ናቸው፡፡ ይህ የተቀናጀ የልማት ፕሮጀክትም ይህንኑ የሚያሳይ ነው፡፡ የእናቶችን የኑሮ ጫና የሚያቀልም ነው” ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ የተገነባው የ“ለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል”ም በዚሁ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት በመዲናዋ ከተከናወኑ ትላልቅ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች የሚጠቀስ ነው፡፡ ማእከሉ በዓመት 10 ሺህ የሚሆኑ ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡና ጎዳና ላይ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ሴቶች ወደ ማእከሉ በመቀላቀል የሚያገግሙበት ሲሆን፤ በዋናነት በዘላቂነት እንዲቋቋሙና የራሳቸውን ገቢ እንዲያገኙ የሚደረግበት ነው፡፡ በማእከሉ የተቀላቀሉ ሴቶች ካሉበት ማህበራዊ ቀውስ ወጥተው የህይወት ክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ በመረጡት ሙያ የተግባር ተኮር ስልጠና ሰልጥነው የራሳቸውን ገቢ እንዲያገኙ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ነው፡፡

ማእከሉ 16 ብሎኮችን ያካተተ ሲሆን፤ 5 ብሎኮች መኝታ ቤት፣ 6 ብሎኮች የማሰልጠኛ ክፍል፣ 1 የህክምና ማእከል፣ ቤተ መፃህፍት፣ መመገቢያ አዳራሽ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ፣ ማገገሚያና ሌሎች ግዙፍ መሰረተ ልማቶችን ይዞ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

በወቅቱ ማእከሉን መርቀው የከፈቱት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ “ፕሮጀክቱ አዲስ አበባ ላይ ከሰራናቸው ፕሮጀክቶች ሁሉ ድንቅ ነው፡፡ ይህ ስራ እንደሃገር ያሉብንን ስብራቶች ለመጠገን እድል የሚሰጥ ነው፡፡ ልጆቻችን ለጎዳና፣ ላልተገባ የህይወት ዘዬ ሲዳረጉ መልሶ የህይወት መስመራቸውን የማቅናት ጉዳይ እንደሃገር ያልተሻገርነው ስብራት ነው፡፡ ባልተገባ መንገድ ህይወታቸውን የሚመሩ ሴቶችን ወደ ተሻለ ሁኔታ ስንመልስ እነሱን ብቻ ሳይሆን የምንጠግነው እንደሃገር ያለብንን የስክነት፣ የማሰብ፣ የማስተዋል፣ አርቆ የመመልከት ስብራትን ነው” ብለዋል፡፡

በማእከሉ ምረቃ እለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ማእከሉ በተለያየ ማህበራዊ ችግር ውስጥ ያሉና ለጎዳና ህይወት ተጋላጭ የሆኑ እህቶቻችን አማራጭ የገቢ ማስገኛ ስራ ላይ መሰማራት እንዲችሉ ብቁ የሚያደርጋቸውን የክህሎት፣ የስነ ምግባር፣ የስራ ባህልና የስራ ስምሪት ጭምር በመፍጠር ነጋቸው ብሩህ ተስፋ የተሞላበት እንዲሆን ለማድረግ ያስችላል፡፡ ማእከሉ ለፆታዊ ጥቃት ሰለባና ለወሲብ ንግድ ተጋላጭ የሆኑ እህቶቻችን መጠጊያ፣ መጠለያ፣ ማገገሚያና የተመሰቃቀለ ህይወታቸውን ዳግም ለመገንባት የሚያስችል ነው፡፡

በማእከሉ የተቀላቀሉ ሴቶች በተለያዩ የህይወት ክህሎትና የሙያ ዘርፎች በተግባር የሰለጠኑ 302 ሴቶች እንዲመረቁ በማድረግም ተስፋ ወዳለው አዲስ ህይወት እንዲቀየሩ ያደረገ ፕሮጀክት ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን ማሳያ አደረግን እንጅ 2016 በጀት ዓመት  የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ፣ የመዲናዋና የሀገርን ገፅታ ከፍ ያደረጉ በርካታ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑበት ነው፡፡ የቃሊቲ-ቱሉ ዲምቱ-ቂሊንጦ መንገድ ተሻጋሪ ድልድዮች፣ ግዙፍ የግብርና ምርቶች ማከፋፈያ የገበያ ማዕከላት፣ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የገበያ ማዕከልና ሌሎች ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል፡፡ አዳዲስና ከባለፈው በጀት ዓመት የተሻገሩ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በበጀት ዓመቱ በመንግስትና በበጎ አድራጊዎች ድጋፍ በአጠቃላይ 18 ሺህ 91 ኘሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ ተችሏል፡፡

በሰገነት አስማማው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review