የሚያጋጥሙንን ትንኮሳዎች በአጭር ለመቅጨት የውስጥ ችግራችንን መፍታትና ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል- አምባሳደር ሬዳዋን ሁሴን

You are currently viewing የሚያጋጥሙንን ትንኮሳዎች በአጭር ለመቅጨት የውስጥ ችግራችንን መፍታትና ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል- አምባሳደር ሬዳዋን ሁሴን

AMN – ጥቅምት 19/2017 ዓ.ም

የሚያጋጥሙንን ትንኮሳዎች በአጭር ለመቅጨት የውስጥ ችግራችንን መፍታትና ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ የብሄራዊ እና ደህንነት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ፡፡

አምባሳደሩ በመከላከያ ዋር ኮሌጅ ተገኝተው በሀገራዊ እና ቀጠናዊ የደህንነት ጉዳዮችና ስጋት ትንተና ዙሪያ ለ3ኛ ዙር መደበኛ ተማሪዎች ገለፃ አድርገዋል።

የአንድን ሀገር ብሄራዊና ታሪካዊ ስጋት መለየትና መተንተን ግልፅ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ለመቅረፅ ብሎም በቂ ምላሽ መስጠት የሚችሉ የማስፈፀሚያ መሳሪዎችን ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

የሀገራችንን ብሄራዊ ደህንነት ለመጠበቅ በእዉቀትና በኢኮኖሚ መጎልበት እና የህዝብን ሁለንተናዊ ደህንነትና አንድነት በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባ መሆን እንዳለበት የገለፁት አምባሳደር ሬዳዋን ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከድህነትና ከተረጅነት መላቀቅ በመላቀቅ አቅማችንን ማጎልበትና ወደ ተሻለ ደረጃ መሻገር ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

በውስጥና በውጭ የሚያጋጥሙንን ትንኮሳዎች በአጭሩ ለመቅጨት የውስጥ ችግራችንን መፍታትና ተባብሮ መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል አምባሳደር ሬድዋን።

ሀገራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በጎራና በመንደር ሳንከለል በአንድነት ሆነን የኢትዮጵያን ልዕልና ማስጠበቅ እንደሚገባ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የአንድን ሀገር ዳር ድንበር እና ብሄራዊ ደህንነትን ለማሥጠበቅ የሁሉም ማህበረሰብ ርብርብ እና ዙሪያ መለስ ተሳትፎ ወሳኝነት ሥለመሆኑም አስረድተዋል።

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ቡልቲ ታደሰ በበኩላቸው ብሄራዊ ደህንነትን ለማስጠበቅ የዜጎች ንቁ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው ለተሳትፎው እንደ ሀገር በአንድነት መቆምና በሀገር ፍቅር ስሜት መነሳሳት አለብን ማለታቸውን ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review