AMN – ጥቅምት 21/2017 ዓ.ም
የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት አመራሮች እና ሠራተኞች በአዲስ አበባ የተከናወኑ እና በሒደት ላይ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል።
አመራሮቹ እና ሠራተኞቹ በአራዳ፣ ልደታ፣ ቂርቆስ እና ቦሌ ክፍለ ከተሞች በመጀመሪያው ምዕራፍ የተጠናቀቁ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን እና በሁለተኛው ምዕራፍ በመሠራት ላይ ያሉትን እንዲሁም የወንዝ ዳርቻ ልማቶችን ተመልክተዋል።
የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እናት ዓለም መለስ የተሠሩትን ሥራዎች እና አጠቃላይ ሒደቱን በተመለከተ ማብራሪያ እና ገለጻ አድርገዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራዎቹ ጥራታቸውን የጠበቁ እና ለረጅም ዓመታት እንዲያገለግሉ በከፍተኛ ጥናት የተሠሩ እና በመሠራት እንዳሉ ወ/ሮ እናት ዓለም በዚሁ ወቅት ተናግረዋል።
በተለይ የፍሳሽ አወጋገድ እና የመንገድ ደኅንነት ትኩረት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን እና በአብዛኛው አካባቢዎች ነባር ሕንፃዎች ባሉበት ሆነው የኮሪደር ሥራው እንዲሳለጥ መደረጉን አብራርተዋል።
በዚህም ሰፊ የትራፊክ እንቅስቃሴ ባለባቸው አካባቢዎች ምቹ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እንዲኖር ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ የሚዲያ አመራሮቹ እና ሠራተኞቹ በበኩላቸው፣ በተመለከቱት ነገር በእጅጉ ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ፣ “እንደዚህ የዘመነ አኗኗር ለኛ ይገባናል” የሚል አስተሳሰብን ያሰረፀ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።
ከመንገድ ግንባታው ባሻገር የወንዝ ዳር ልማት መከናወኑ፣ ውብ ግንባታዎች እና አገልግሎት መስጫዎች መካተታቸው ሥራውን ሙሉ እንደሚያደርጉም ጠቅሰዋል።
በዮናስ በድሉ