የዓለም የኢኮኖሚ ስርዓት ፈጣንና ውስብስብ ለውጦችን ማስተናገድ ከጀመረ ሰነባብቷል። ዓለም ጎራ ለይታ ያካሄደቻቸው ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች፣ ይህንኑ ተከትለው የተፈጠሩ ክስተቶችና የኃይል አሰላለፎች ለኢኮኖሚው አለመረጋጋት መንስኤ እንደሆኑ የዘርፉ ሊሂቃን ይናገራሉ። ከጦርነቶቹ ማብቃት በኋላ ስፍራውን የወሰደው ቀዝቃዛው ጦርነት ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አወሳስቦታል ተብሎ ይታመናል። እነዚህ ግዙፍ ክስተቶች የዓለምን መልክ ቀይረውታል ሊባል ይችላል። በርካታ ሀገራት በሁለትና ከዚያ በላይ በሆነ ቦታ ተከፍለዋል፣ የቴክኖሎጂ ፉክክሩ ተጠናክሯል፣ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ስጋት ሆኗል፣ ወረርሽኞች ተበራክተዋል፣ ጦርነቶች እዚህም እዚያም ተለኩሰዋል። በጥቅሉ ዓለም በእነዚህ ተለዋዋጭ ፈተናዎች ውስጥ ከርማለች።
ይህም የዓለም ኢኮኖሚ ላይ በአዎንታዊም በአሉታዊም ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ቴክኖሎጂ የፈጠረው ትስስር፣ የሀገራት በትብብርና በፉክክር መስራት ዓለምን ወደ አንድ መንደርነት አምጥቷል።ይህም በአንድ አካባቢ የሚፈጠር ዕድልም ሆነ ችግር ለሌሎች ጭምር የሚተርፍበት ሁኔታ እንዲኖር አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያም የዓለም አካል እንደመሆኗ የዚህ ውጤት ሰለባ ከመሆን አልዳነችም። ተከታታይ እድገት ስታስመዘግብ ቆይታለች እየተባለ ቢነገርም በብዙ መልኩ ዕደገቱ ጤናማ ስላልነበር በጊዜ ሂደት ለውስብስብ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመዳረግ ተገድዳለች። በተለይ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የኑሮ ውድነት ፈተናዎቿ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ከችግሩ ለመውጣትም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርካታ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች። ለአብነትም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ቀርጻ እየተገበረች መሆኑ ይታወቃል። ኢትዮጵያ ታምርት፣ ገበታ ለሀገር፣ የሌማት ትሩፋትና መሰል ንቅናቄዎችንም በማካሄድ ላይ ትገኛለች።
በቅርቡም ይፋ ከተደረገው አዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ በተጨማሪ ሰሞኑን ደግሞ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተደርጎ ከሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር መግባቱ ይታወሳል፡፡ ማሻሻያው በሚቀጥሉት 4 ዓመታት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በአማካይ በ8 በመቶ ያህል እንደሚያሳድገው ይታሰባል።
በተጨማሪም የዋጋ ንረትን ወደ 10 በመቶ እንደሚያወርደው፣ የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለውን ድርሻ 11 በመቶ እንደሚያደርሰው፣ የመንግስት ዕዳን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለውን ድርሻ ወደ 35 በመቶ ዝቅ እንደሚያደርገው፣ የወጪና የገቢ ንግድን ዋጋ ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያሳድገው፣ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን ወደ 8 ቢሊዮን ዶላር እንዲደርስ እንደሚያግዝ፣ የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ የመጠባበቂያ ገንዘብ ክምችት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያደርሰው ተመላክቷል፡፡
የኢፌዴሪ ፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ ባለፉት አምስት ዓመታት በተደረገ እልህ አስጨራሽ ድርድር በአጠቃላይ ከ27 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡ ውጤቱ የኢትዮጵያን መንግስት የፖሊሲ ነፃነት በማይገድብ ሁኔታ የተገኘ መሆኑን ጠቅሰው፣ ገንዘቡ በቅርቡ መምጣት እንደሚጀምርም ገልፀዋል፡፡
ለመሆኑ ማሻሻያው በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረው ትርጉም ምንድን ነው? ማሻሻያውን ተከትሎ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የሚገኘው የውጭ ምንዛሬስ ምን አንድምታ አለው? ስንል የዘርፉን ምሁራን ጠይቀናል፤
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ተፈራ በሪሁን (ዶ/ር)፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተራዘመ ጊዜ ውስጥ የኢኮኖሚ ስብራቶችን ጠግኖ የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊ ስርዓትን እንደሚፈጥር ያነሳሉ፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለኢትዮጵያ የሚለቅቋቸው ብድሮችና ድጋፎች ለበርካታ ዓመታት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተግዳሮት ሆኖ የቆየውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማቃለል ረገድ የሚኖረው ሚና በቀላሉ እንደማይታይ ጠቁመው፣ ይህም በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ የምጣኔያዊ ሀብት ከፍተኛ ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በሩህተስፋ (ዶ/ር)፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተለያዩ ምክንያቶች የሚደረግ መሆኑን ጠቁመው፣ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ አንፃር አስፈላጊነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ካለችበት ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አንፃር አንዳንድ የኢኮኖሚ ምሶሶዎችን ማስተካከል የውዴታ ግዴታ እንደሚሆንና አሁን የተደረሰበት ውሳኔም ተገቢነት ያለው መሆኑን አክለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ሲመቻቹ መቆየታቸውን የጠቀሱት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፣ ለአብነትም በመቋቋም ሂደት ላይ ያለው የካፒታል ገበያ ስርዓት አንዱ እንደሆነና ይህም ኩባንያዎች ካፒታል በሚፈልጉበት ጊዜ ባንክ ሄዶ መበደር ብቻ ሳይሆን ገበያ ውስጥ ገንዘብ ማግኘት የሚችሉበትን ዕድል የሚሰጥ አሰራር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በተለይ ከዓለም አቀፍ ባለሀብቶች በአክሲዮን ሽያጭና ግዢ አማካኝነት የውጭ ምንዛሬ እንደልብ መንቀሳቀስ የሚችልበትን ዕድል የሚፈጥር አሰራር መሆኑን አብራርተዋል። ይህ አሰራር ኢትዮጵያ ያሏት የተፈጥሮ ሀብቶች አግባብና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በሚችሉበት ልክ ወደ ጥቅም የሚገቡበትን መንገድ እንደሚፈጥርም ገልፀዋል፡፡
እንደ ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) ማብራሪያ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የሚፈጠረው ምጣኔ ሀብታዊ ሁኔታ የውጭ ባንኮች መዋዕለ ነዋያቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ በር ይከፍታል፡፡ እንደ ውሃ፣ መሬት፣ ማዕድን የመሰሉ ኢትዮጵያ ባሏት ሀብቶች ላይ በሰፊው እንዲሰማሩ ያስችላል፤ ይህም ከፍተኛ ልምድና የገበያ ሰንሰለት ያላቸው ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ማምረትን እንዲመርጡ በማድረግ ከፍተኛ በሆነ ደረጃ የውጭ ንግድ ዘርፉን ያሳድገዋል ብለዋል፡፡
ገበያ መር በሆነ ኢኮኖሚ ውስጥ ቋሚ የገንዘብ ዋጋ አይኖርም ያሉት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፣ ብር በዶላር ያለው ዋጋና የወለድ ምጣኔው በየጊዜው ከፍም ዝቅም ሊል እንደሚችል ጠቅሰው፣ ማሻሻያው በተደረገባቸው ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የምንዛሬው መጠን ሊጨምር ቢችልም በቋሚነት እንደዚያው ይቀጥላል ማለት እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ አቅም እየጎለበተ በሄደ ቁጥር የውጭ ምንዛሬው እንደሚቀንስም አውስተዋል፡፡ ይህን ነጥብ ሲያብራሩም፣ “የዓለም ባንክ፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) እና ሌሎች አካላት ለኢትዮጵያ እየለቀቁላት ያለው ብድርና ድጋፍ ባንኮች በቂ የውጭ ምንዛሬ አግኝተው ወደ ጥቁር ገበያ የሚሄደውን የገንዘብ ፍሰት በመቀነስ ኢኮኖሚውን ከማረጋጋት አንፃር ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል” ብለዋል፡፡
አክለውም፣ “የሚለቀቀው ብድርና ድጋፍ የኢትዮጵያን የውጭ ንግድ ከማጠናከር፣ ምርታማነትን ከማሳደግ፣ የምርት አቅርቦትና ፍላጎትን ከማመጣጠን አንፃር ሚናው ቀላል አይሆንም፡፡ ምክንያቱም የሀገር ውስጥ ሸማች የምርት ፍላጎት በቀላሉ ሊስተናገድ የሚችልበት መንገድ ስለሚፈጠር የውጭ ምንዛሬ ፍላጎቱ እየረገበ ይሄዳል” የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ተፈራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የዜጎችን አጠቃላይ ደህንነት ለማረጋገጥ ከሚተገበሩ የመፍትሔ አማራጮች መካከል እንደ አንዱ ሊወሰድ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ይህን ሀሳብ ሲያብራሩም፣ “መንግስታት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ደህንነት ለማረጋገጥ ሶስት ዓላማዎች ያሏቸውን እርምጃዎች ይወስዳሉ። አንደኛው አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት፣ ሁለተኛው የስራ አጥነትን መቀነስ፣ ሶስተኛው ደግሞ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ናቸው፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውም ይህንኑ ለማድረግ የተወሰነ ነው” ብለዋል፡፡
ማሻሻያውን ተከትሎ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ በፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ የዋጋ ንረቱ እንዲቀንስ፣ የሥራ ዕድል እንዲሰፋና አጠቃላይ ኢኮኖሚው እንዲያድግ ያደርጋል ባይ ናቸው ተፈራ (ዶ/ር)።
የብር ዋጋ ሲቀንስ ዜጎች የሀገር ውስጥ ምርትን በስፋት እንዲጠቀሙ ያስገድዳል በማለት፣ ሂደቱ የገቢ ንግድን በመገደብ የወጪ ንግድን እንደሚያበረታታ፣ አስፈላጊነታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች እንዲቀንሱ በማድረግ የንግድ ሚዛንን እንደሚያስጠብቅ ገልፀዋል፡፡ አሁን መደረግ ያለበት የሀገር ውስጥ ምርታማነትን ማሳደግ ነው ሲሉም መክረዋል፡፡
እንደ ተፈራ (ዶ/ር) ማብራሪያ፣ ማሻሻያው ተኪ ምርቶች ላይ እንዲተኮር ያስችላል፡፡ የውጭ ባለሀብቶች ጥቂት ዶላር ይዘው መጥተው ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት የማድረግን ዕድል ስለሚያገኙ በብዛት ይመጣሉ፡፡ ይህም በጊዜ ሂደት የሀገር ውስጥ ምርታማነት አድጎ ለውጭ ገበያ የሚቀርብን ምርት ያበዛል፡፡ ብዙ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ደግሞ የውጭ ምንዛሬን ያሳድጋል፤ በሀገር ውስጥ ደግሞ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ፍላጎት እንዳይኖር ስለሚያደርግ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት እንዲቀንስ ያስችላል ማለት ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ያደረገችው ማሻሻያም በረጅም ጊዜ ውስጥ ይህን ውጤት እንዲያስገኝ ታስቦ ነው፡፡
ማሻሻያው ለጊዜው የኑሮ ውድነትን እንደሚያስከትል እሙን ነው ያሉት ተፈራ (ዶ/ር)፣ አላስፈላጊና ተገቢነት የጎደለው ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡ አክለውም የሚመጣው የውጭ ምንዛሬ የህብረተሰቡን ኑሮ መቀየር በሚችሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲውል አበክሮ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች አንፃር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አስፈላጊ እንደሆነ የጠቆሙት ተፈራ (ዶ/ር)፣ አሁን ባለው ሁኔታ ከዚህ በላይ መቆየት ለከፋ ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅሎሾች የመዳረግ ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ሀገራት በዚህ ስልት ተጉዘው ሊደርስባቸው ይችል ከነበረ ውድቀት መዳናቸውን በማውሳት፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በአግባቡ ከተተገበረ ለተሻለ ውጤት የሚያበቃ መሆኑን ከሲንጋፖር፣ ህንድ እና ሌሎች መሰል ሀገራት መማር እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡
ተፈራ (ዶ/ር) የብር ዋጋ ከዶላር አንፃር መቀነሱ የሚያሳስብ ጉዳይ አለመሆኑን ሲያስረዱ፣ የጃፓን፣ የሩሲያ፣ የደቡብ ኮሪያ እና ሌሎች ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አቅም ያላቸው ሀገራት ገንዘብም ከዶላር አንፃር ከኢትዮጵያ ብር በላይ የወረደ ዋጋ እንዳላቸው ማሳያ አድርገዋል፡፡ ዋናው ቁም ነገር የኢኮኖሚ ማሻሻያ አድርገው ለስኬት የበቁ ሀገራትን ተሞክሮ ይዞ በተቻለ መጠን ኢትዮጵያ ያደረገችው ማሻሻያ ስኬታማ እንዲሆን በርትቶና ተጋግዞ መስራት ያስፈልጋል ሲሉም መክረዋል፡፡
በተመሳሳይ ቆስጠንጢኖስም (ዶ/ር)፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተገቢነትና ስኬታማ ሊሆን የሚችልበትን ምክንያት ሲያብራሩ፣ ኢትዮጵያ አስቀድማ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ማድረጓና ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት መሆኗን አንስተዋል።
እስከ አሁን ባሉት ጊዜያት ውስጥ በሺህ ኪሎ ሜትር የሚቆጠር መንገድ መዘርጋቷ፣ ሰፋፊ የገበያ መዕከላትን ማዘጋጀቷ፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ነፃ የንግድ ቀጣናዎች፣ ግድቦች፣ የኃይል ማሰራጫዎች፣ ከ50 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ያሏት ሀገር እንደመሆኗ የኢኮኖሚ ማሻሻያውና ይህንኑ ተከትሎ የሚመጣው የውጭ ምንዛሬ ለኢኮኖሚው ትልቅ መስፈንጠሪያ ይሆናል ብለዋል፡፡
ከመንግስት የሚጠበቀው በብድርና ድጋፍ የሚመጣውን ገንዘብ በትክክል በልማት ላይ የሚውልበትን ዕድል ማመቻቸት እንደሆነ ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) መክረዋል፡፡ በተለይ ገንዘቡ ባንኮች እጅ ገብቶ በህጋዊ የንግድ ስራ ላይ ለተሰማሩ ባለሀብቶች እንዲደርስ እና እነሱም በትክክለኛው መንገድ ለተባለው ጉዳይ ብቻ ማዋላቸውን በመከታተል ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
በተካልኝ አማረ