የሶማሌ ክልል የምክክር ባለ ድርሻ አካላት የክልሉን አጀንዳ ለኮሚሽኑ አስረከቡ

You are currently viewing የሶማሌ ክልል የምክክር ባለ ድርሻ አካላት የክልሉን አጀንዳ ለኮሚሽኑ አስረከቡ

AMN – ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስተባባሪነት በሶማሌ ክልል ሲካሄድ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ዛሬ ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም ተጠናቋል።

ኮሚሽኑ በክልሉ ከጥቅምት 4/2017 ዓ.ም ጀምሮ በሁለት ምዕራፎች የምክክር መድረኩን ሲያከናውን ቆይቷል።

ከጥቅምት 4-6/2017 ዓ.ም በተካሄደው የመጀመሪያው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ በጅግጅጋ፣ በጎዴና በዶሎአዶ ማዕከላት የማህበረሰብ ወኪሎች ምክክር መካሄዱ ይታወሳል።

በዚህ የምክክር መድረክ በጅግጅጋ ማዕከል ከ1ሺ በላይ፣ በጎዴ ከ650 በላይ እንዲሁም በዶሎ አዶ ደግሞ ከ350 በላይ ወኪሎች ተሳታፊ ነበሩ።

የማህበረሰብ ወኪሎች የምክክር መድረክ ከተጠናቀቀ በኃላ ባሳለፍነው እሁድ ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም የክልሉ ባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ መጀመሩም ይታወቃል ፡፡

በዚህ የምክክር መድረክ ከ1ሺ 200 በላይ የሚሆኑ የማህበረሰብ ወኪሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወኪሎች፣ የክልሉ መንግስት ተወካዮች፣ የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ወኪሎች እንዲሁም የልዩ ልዩ ተቋማትና ማህበራት ተወካዮች ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡

የባለድርሻ አካላቱ ከጥቅምት 10/2017 ዓ.ም ጀምረው ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ አጀንዳዎችን በውይይት ለይተውና አደራጅተው ዛሬ ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም ለኮሚሽኑ አስረክበዋል።

የክልሉን አጀንዳዎች ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) እና ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም ከተወካዮቹ ተቀብለዋል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርአያ (ፕሮፌሰር) በክልሉ የተካሄደው ምክክር በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት በኮሚሽኑ ስም አመስግነዋል።

የክልሉን የምክክር መድረክ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ፣ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ እና ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም በበላይነት ሲያስተባብሩት መቆየታቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያሳያል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review