AMN – ታኀሣሥ 10/2017 ዓ.ም
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አ/ማ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትን ደህንነት ለማስጠበቅ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።
የፌደራል ፖሊስ ከተሰጠው ተልዕኮ ውስጥ አንዱ የሀገሪቱን መሰረታዊ ተቋማትን መጠበቅ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ ለኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርትም የተሰጠውን ትኩረት በመገንዘብ ራሱን የቻለ መምሪያ በማቋቋም የጥበቃ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ተገልጿል።
ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት ያላቸውን አቅም አቀናጅቶ በመጠቀም ውጤታማ የሆነ የጥበቃ ሥራ ለመስራት እንደሚያስችል ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እንዳሉት የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት የሀገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ ዋና መስመር እና ከወደብም ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገልጿል።
ኮሚሽነሩ ስምምነቱ በተናጠል ሲሰራ የነበረውን አሰራር በማስቀረት በትብብር ለመስራት የሚያስችል መሆኑን አንስተው የአገልግሎቱን ደህንነት ለማስጠበቅ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) በበኩላቸው፣ አክሲዮን ማህበሩ ትርፋማ እንዲሆን እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህንን ለማሳካትም ዋነኛ የሆነውን የደህንነት ችግር ለመፍታት ስምምነቱ መደረጉን ገልጸው ስምምነቱ ተቋሙ በሙሉ አቅሙ እንዲሰራ የሚያስችል ነው ማለታቸውን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።