የተራሮች ውለታ

ተራሮች በኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ውስጥ ትልቅ ስፍራ አላቸው፡፡ በማህበረሰቡም ሆነ በኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ውስጥ ግርማ ሞገስ፣ ጀግንነት፣ ቅድስና፣ ታላቅነት፣ ከፍታ… በተራራ ይመሰላሉ፡፡ ተራሮች ከመሬት ከፍ ብለው የሚታዩ፤ ሰማይን ለመንካት የሚንጠራሩ በመሆናቸው ግርማ ሞገስ አላቸው፡፡ ታላቅነታቸው በግልጽ ስለሚታይ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ይከበራሉ፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍም በፈረንጆቹ ታህሳስ 11 የተከበረውን ዓለም አቀፍ የተራሮች ቀንን መነሻ በማድረግ ስለ ተራሮች የተሰሩ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎችን በጨረፍታ ልናስቃኛችሁ ወድደናል፡፡

ተራሮች የነጻነት ተምሳሌት ናቸው። ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በውጭ ሃይሎች ወረራ ሲያጋጥማት፣ኢትዮጵያውያን የሃገራቸውን ነጻነት ለማስጠበቅ ተራሮችን እንደምሽግ ተጠቅመዋል፡፡ ለአብነትም አድዋ ላይ የሶሎዳ ሰንሰለታማ ተራሮች ለዚህ ጥሩ ምስክር ናቸው፡፡ ከጣሊያን ጋር በተደረገው ጦርነት ዛሬም ድረስ ስሙ ገንኖ የሚነሳው አምባ-አላጌ (የአላጌ ተራራ) ሌላኛው ምስክር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ተራሮች የኢትዮጵያን ነጻነት አስጠብቆ በማስቀጠል ሂደት ውስጥ ግዙፍ ስፍራ የያዙ በመሆናቸው የነጻነት ተምሳሌት ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ተራሮች መካከል የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከፊል ገፅታ

ተራሮች የቅድስና ተምሳሌቶች ናቸው። በተለይ በክርስትና ዕምነት ውስጥ ተራሮች ወይም አምባዎች ትልቅ ሥፍራ አላቸው፡፡ ተራሮች እንደ ገዳም ላለ ለተቀደሰ ሥፍራነት  የሚመረጡ፣ እንደ ደብረ ታቦር ተራራ ያሉት ደግሞ የፈጣሪን ክብር የሚገለጥባቸው ሥፍራዎችም ናቸው፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን በ‘እሳት ወይ አበባ’ የግጥም መድብሉ ላይ ያሰፈረው “መሸ ደግሞ አምባ ልውጣ!” የተሰኘው ግጥሙ ተራራን የቅድስና ስፍራ አድርጎ ነው የሳለው፡፡

የተራሮች ቀን ሲታሰብ

ከፈረንጆቹ 2003 አንስቶ (UNESCO) የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በየዓመቱ ታህሳስ 11(Desember 20) ቀን የተራሮች ቀን እንዲከበር ውሳኔ አሳልፏል። ምክንያቱም ተራሮች ልናከብራቸው የሚገቡ የተፈጥሮ ዕንቁዎች በመሆናቸው ነው ይላል:: ዩኔስኮ በይፋዊ ገጸ-ድሩ ቀኑን አስመልክቶ ባሰፈረው ጽሑፍ። 15 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ መኖሪያ የሆኑት ተራሮች፣ ግማሹን የዓለም የብዝሃ ሕይወት ቦታዎች ያስተናግዳሉ። የንጹህ ውሃን ጨምሮ ለሌችም ለዕለት ተዕለት ኑሮ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለሰው ልጆች ይሰጣሉ፡፡ይህም የእርሻ ሥራን ለመጠበቅ እና ንጹህ ኃይል እና መድሃኒቶችን ለማቅረብ እንደሚረዱም የዩኔስኮ መረጃ ያሳያል፡፡

እንደ አለመታደል ሆኖ ይላል የዩኔስኮ መረጃ፣ ተራሮች በአየር ንብረት ለውጥ፣ከመጠን በላይ ብዝበዛ እና ብክለት ምክንያት ስጋት ላይ ናቸው፡፡ ይህም ለሰዎች ህይወት እና ለፕላኔታችን ያለውን ስጋት ይጨምራል ይላል፤ መረጃው፡፡ የዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ሙቀት እየጨመረ በሄደ ቁጥር የተራራ በረዶዎች ይቀልጣሉ፡፡ የንጹህ ውሃ አቅርቦቶችን ይጎዳሉ፡፡ በዚህም በተራራ ዙሪያ የሚኖሩ ህዝቦችና ራሳቸው ተራሮች ከባድ ፈተና ላይ እንደሚወድቁ ዩኔስኮ በመረጃው ጠቅሷል፡፡

እንደ ዩኔስኮ መረጃ ከሆነ፣ከተራራ ጋር የተያያዙ ውስብስብ ጉዳዮችን ለመፍታት ፈጠራ አስፈላጊ ነው። ይህ ደግሞ የቴክኖሎጂ እድገቶችን እና እንደ የአየር ንብረት-ዘመናዊ ግብርና ያሉ ችግሮችን መፍታትን ያካትታል። ተራሮች የአየር ንብረት ለውጥን ጫና እንዲቋቋሙ የሚሰሩ ስራዎች፣ ቀጣይነት ያለው አስተማማኝ ልማት ለመከወን እና ተጋላጭነትን ለመቀነስ መላመድ የግድ ይሆናል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሃገራት በየጊዜው የሚከውኗቸው የአረንጓዴ ልማት ስራዎች የተራሮችን ደህንነት ለመጠበቅ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ነው መረጃው የሚገልጸው፡፡

ተራሮችና ኪነ ጥበብ

ተራሮች በተለይ በሥነ ጽሑፍና ሙዚቃ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ጀግንነትን፣ ነጻነትን፣ ናፍቆትን፣ ቅድስናን፣ ግርማ ሞገስን…ለመግለጽ ተራሮች እንደ ተለዋጭ ዘይቤ ያገለግላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለይ በሥነ ግጥም ውስጥ እንደተራሮች ያሉ መልክዐ ምድሮች የግጥም ዘውግ ጭምር ናቸው፡፡

እንደሚታወቀው የሥነ ጽሑፍ ምሁራን የተለያዩ የሥነ ግጥም ዘውጎች (አይነቶች) እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡ ከእነዚህ የግጥም አይነቶች መካከል አንዱ “ገጸ ምድራዊ ግጥም” (Topographical poetry) ነው። የሥነ ጽሑፍ ምሁሩ ብርሃኑ ገበየሁ 2001 ዓ.ም ባሳተመው “የአማርኛ ሥነ ግጥም” በተሰኘው መጽሐፉ ገጸ-ምድራዊ ግጥምን ሲያብራራው፣“ወንዞችን፣ከተሞችን፣ ተራሮችን የሚስሉ ግጥሞች ናቸው፡፡…የገጸ ምድር ግጥሞች ይበልጥ መታወቂያቸው የአገሬውን ታሪካዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ እሴቶች አግዝፈው የማሰማት ግብና ዓላማ አላቸው” በማለት አስፍሯል፡፡

በአማርኛ ሥነ ግጥም ውስጥ ገጸ ምድራዊ ግጥሞችን አዘውትሮ የሚደርስ ገጣሚ ጸጋዬ ገብረመድህን ነው፡፡ ከሱ ግጥሞች አባይ፣ ሐረር፣ አንኮበር፣ አይ መርካቶ፣ አዋሽ፣ ሊማሊሞ….የዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ እስኪ ከ’እሳት ወይ አበባ’ የግጥም መድብል ውስጥ ስለ  ሊማሊሞ ተራራ የተቀኘው ግጥሙ እዚህ ጋ እንጥቀሰው፤

የሰማይ የምድሩ ኬላ፣ የየብስ የጠፈሩ ዋልታ

አይበገር የአለት ጣራ፣ አይመክተው መከታ

ሊማ-ሊሞ አድማስ ሰበሩ፣ በጎማ ፈለግ ይፈታ?

በትሬንታ እግር ይረታ?…

ሊማሊሞ የሰሜን ተራራዎች አካል የሆነ በደባርቅ እና ድብ ባህር መካከል የሚገኝ ተራራ ነው። በተጨማሪም ሰሜን ኢትዮጵያን ከመሃል አገር ጋር የሚያገናኘው እና በአስፈሪነቱ የሚታወቀው አውራ ጎዳና በዚህ በሊማሊሞ ተራራ በኩል ነው የሚያልፈው።

ገጣሚና ጋዜጠኛ ነቢይ መኮንን የፀጋዬን ሊማሊሞ ግጥም በተነተነበት አንድ ጽሑፍ፣ “ሊማሊሞ የምድር ኬላ ነው። ሊማሊሞ ለምድር ዘብ የቆመ ነው። ሊማሊሞ ለጠፈሩ ደግሞ ዋልታ ሆኖ የቆመ ነው። ሊማሊሞ የማይበገር አለት ነው። መከታና ጋሻ ነው። ሊማሊሞ በዐይናችን የምናየውን ሰፊ አድማስ ሰብሯል። ወደ ሽቅብ ከሰማዩ ጋር ስናየው ደሞ ሊማሊሞን አድንቆ ሰው አድርገን ፊታችን እንድናይ ለማድረግ ከደመናው በላይ አልፎ ይታየናል ይለናል። አለፍ ብሎም ከሰማይ ጋር ይለካካል። ጉም እንደቀሚስ አጥልቋል።”

ሌላኛው የሃገራችን ታላቁ ገጣሚና ሰዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ “አገሬ” በተሰኘው ግጥሙ የኢትዮጵያን ምልክዐ ምድርን ይናፍቃል፡፡ ጀርመን ሃገር ውስጥ ሆኖ በጻፈው በዚህ ግጥሞ የሃገሩን ተራራ፣ ፀሐይ፣ ሸለቆውን ረባዳው ደጋግሞ ያወሳል፡፡ ከልጅነትና ከነጻነት ጋር በማስተሳሰር እንዲህ ተቀኝቷል፤

አገሬ ውበት ነው፤

ለምለምና ነፋስ የሚጫወትበት፣

ፀሐይ የሞላበት፤ ቀለም የሞላበት፡፡

አገሬ ቆላ ነው፤ ደጋ ወይናደጋ

እዚያ ብርሃን አለ ሌሊቱ ሲነጋ፡፡

አገሬ ተራራ፣ ሸለቆ ረባዳ፣

አገሬ ጅረት ነው ገደልና ሜዳ፡፡

አልፎ አልፎ ተራራዎች ማዶና ማዶ ያሉ ማህበረሰቦችን ወይም ግለሰቦችን የሚያለያዩ ድንበሮች ተደርገው በአንዳንድ የኪነ ጥበብ ስራዎች ቀርበዋል፡፡ ታዲያ ይህ ድንበር የትዝታ ድንበር ነው፡፡ የመናፈቅ ድንበር ነው። እንዲሁም የመተጣጣት ድንበርም ጭምር ነው፡፡ ወጣቱ ሙዚቀኛ ዳንኤል ዘውዱ “ማዶ ተራራ” ሲል ባቀነቀነው ሙዚቃ ይህንኑ ነው አጉልቶ ያሳየው፤

ያ ማዶ ተራራ ጋራው ከለለሽ

ያ ማዶ ተራራ ጉሙ ሸፈነሽ

እኔ እንዳለሁ አለሁ፤ አንቺ እንደምነሽ፡፡

ጠዋት ማታ ትዝታ

ጠዋት ማታ እንጉርጉሮ

ልቤ በትውስታሽ፤ በናፍቆትሽ ታስሮ፡፡

በአጠቃላይ ተራሮች የውበት፣ የጀግንነት፣ የነጻነትና የቅድስና ተምሳሌት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም እንደ ራስ ዳሽን (ራስ ደጀን)፣ ዘቢደር፣ አምባላጌ፣ ሶሎዳ፣ የባሌ ተራሮች…ባለቤት ነች፡፡ በተለይ በደጋና ወይናደጋው የኢትዮጵያ ክፍል ላይ በርካታ ተራሮች በመኖራቸው ኢትዮጵያውያን ከተራሮች ጋር ያላቸው ትስስር የጠበቀ አድርጎታል፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review