የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

You are currently viewing የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

AMN- ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት ምክትል ተወካይ እና የኢትዮጵያ ፕሮግራም ኃላፊ ቻርለስ ኩዌሞይ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይታቸውም ሁለቱ ተቋማት በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ እና ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዙ ሀገራዊ እንቅስቃሴዎች በጋራ በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

ሚኒስትር ዴኤታው የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኢትዮጵያ እያከናወነቻቸው ለሚገኙ የሰብዓዊ መብት ማስከበር ተግባራት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ዝግጅት ሂደት ሙያዊ ድጋፍ በመስጠትና ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ልምድ እንድትቀስም ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩን አመልክተዋል።

ተመድ የሽግግር ፍትህ ትግበራ ምዕራፍ ሂደቱን ውጤታማነት ለማረጋገጥ እና ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ግዴታዎች ለመወጣት ለምታደርገው ጥረት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት ምክትል ተወካይ ቻርለስ ኩዌሞይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆና በመመረጧ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ አባል መሆኗ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚከናወኑ የሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር ተግባራት የሚኖረው ሚና ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ በሚኖራት ቆይታ መድረኩን በሚገባ ትጠቀምበታለች ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ተመድ በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅት ሂደት እስከ አሁን ሲያደርግ ከነበረው ድጋፍ በተጨማሪ በቀጣይ የፖሊሲ ትግበራ ምዕራፍም ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ግዴታዎቿን ለመወጣትና የፍልሰተኞችን መብት ለማስከበር ለምታደርገው ጥረት ድጋፉን እንደሚቀጥል ተወካዩ መግለጻቸውን ከፍትሕ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review