የአብሮነት ነፀብራቅ

“ስጦታ መሰጣጠት ማለት አንዱ ለአንዱ ‘በእኔ ሕይወት ውስጥ ቦታ አለህ’ ማለት ነው”

በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎጂ መምህርና ተመራማሪ ጉተማ ኢማና (ዶ/ር)

የሀገሬ ሰው “የስጦታ ፈረስ ጥርሱ አይታይም” ይላል፡፡ እውነት ነው፤ ፈረሱ ቢሻው ያርጅ፣ ቢለውም ይሰበር፤ ዋናው ነገር አብሮነትን፣ መተሳሰብን እና ፍቅርን መሰረት አድርጎ ከልብ የመነጨ የወዳጅ ስጦታ በመሆኑ ዋጋው ከፈረሱ በላይ ነው፡፡ ስለስጦታ ስናነሳ ዓለም በድንቃ ድንቅ መዝገቧ ይህንን እውነት አስፍራለች። በፈረንሳዊው የቅርጻ ቅርጽ ባለሙያ ፍሬድሪክ አውጉስት ባርትሆሊ የተሰራው ሃውልት ሰዎች ለሰዎች የሰጡት የዓለማችን ድንቁ ስጦታ እንደሆነ ይነገራል። ይህ የፈረንሳይ ህዝብ ለአሜሪካ ህዝብ ያበረከቱት ስጦታ ነው።

ሃውልቱ 46 ነጥብ 50 ሜትር ቁመት እና 252 ቶን ክብደት ያለው ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ1885 ከፈረንሳይ ወደ አሜሪካ ተጓጉዞ በጥቅምት 28 ቀን 1886 ተመረቀ። በእግሮቿና በእጆቿ የተበጣጠሰ የባርነት ሰንሰለት እንዲሁም የነፃነት ችቦን የምታሳይ የሴት ምስል ያለው ይህ ሃውልት የአሜሪካ የነፃነት መግለጫ ሆኖ ለዘመን ዘመናት በክብር ቆሟል፡፡ ይህ የነጻነት ሃውልት በኒውዮርክ ውስጥ በጣም ዝነኛ ከሆኑት የቱሪስት መስህቦች አንዱ ሲሆን፣ በትንሹ 4 ነጥብ 44 ሚሊዮን ሰዎች በየዓመቱ ይጎበኙታል። የዓለማችን ድንቃድንቅ ሀቆችን በመመዝገብ በሚታወቀው ጊኒየስ ዎርልድ ላይ ስለመመዝገቡም ድርጅቱ ይፋ ያደረገው መረጃ ያመላክታል፡፡

ዋና መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው ናሽናል ኢንዶውንመንት ፎር ዘ ሂዩማኒቲስ የተሰኘው ተቋምም ዘ ስታቲዩ ኦፍ ሊበርቲ፡ ዘ ሚኒንግ ኤንድ ዩዝ ኦፍ ኤ ናሽናል ሲምቦል በሚል ርዕስ በይፋዊ ትስስር ገፁ ባሰፈረው መረጃም ይህ የአሜሪካ ህዝቦች የነፃነት አርማ የሆነው ሃውልት በተለይ በፈረንሳይና በአሜሪካ ህዝቦች መካከል ዘመን ለተሻገረውና ክፉ ቀን ላላደበዘዘው ጤናማ ግንኙነት ትልቅ አበርክቶ እንዳለውም አመላክቷል፡፡

በርግጥም የአንድ ሀገር ህዝብ ለሌላው ህዝብ ስለሰጠው ስጦታና ከፍ ስላለው ትርጉሙ ስንረዳ ስጦታ ምን ያህል አብሮነትን ማጎልበቻ፣ መለያየትን መርቻ፣ ፍቅርን ማሰንበቻ ድንቅ መሳሪያ እንደሆነች እንገነዘባለን። ያለንበት ወቅት በክርስትና ኃይማኖት አስተምህሮ መሰረት ለሰው ልጆች ሁሉ ድንቅ ስጦታ የተሰጠበት የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል የሚከበርበት ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሰዎች የተለያዩ ስጦታዎችን ይሰጣጣሉ፡፡ ፈጣሪ ለሰው ልጆች እንደሰጠው ውድ ስጦታ አሊያም ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ኢትዮጵያውያኑ ሰብአ ሰገል (ሰብአ ሰገል የግእዝ ቃል ነው። ሰብአ ማለት ሰው ሲሆን፣ ሰገል ደግሞ ጥበብ ማለት ነው።) በመሆኑም የጥበብ ሰዎች ወርቅ፣ እጣን እና ከርቤ እንደሰጡት፤ ኢየሱስም በይሁዳ ቤተልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፣ “እነሆ ሰብአ ሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና” እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፡፡ …“ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው፡፡”

ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፣ ወድቀውም ሰገዱለት፡፡  ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት፡፡” እንዲል አስተምህሮው፣ ይህንን እና ሌሎች ኃይማኖታዊና ማህበራዊ መሰረቶችን መነሻ በማድረግም በዓለማችን በተለይ በገና ሰሞን ስጦታ መሰጣጠት በስፋት ይስተዋላል። በአዲስ አበባም በግለሰብ ደረጃ ያለው ለሌለው አካፍሎ በዓሉን በደስታ ማሳለፍ የተለመደ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ማዕድ ሲያጋሩ

ከዚህ ባለፈም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ማዕድ ማጋራት ባህል እየሆነ መጥቷል። አዲስ ልሳን ጋዜጣ ለመሆኑ የዚህ የመጠያየቅና የመደጋገፍ ባህል ፋይዳው ምን ይሆን? የበለጠ እንዲጎለብትስ ከማን ምን ይጠበቃል? ስትል በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎጂ (የህብረተሰብ ጥናት) መምህርና ተመራማሪ ጉተማ ኢማና ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡

ጉተማ ኢማና (ዶ/ር) እንደ ገና ባሉ በዓላት አንዱ ለሌላኛው ስጦታ የመስጠት ባህል ከጥንት ጀምሮ የነበረና አሁንም ቀጥሎ ያለ ተግባር ነው፡፡ ስጦታ መሰጣጠት ማለት አንዱ ለአንዱ “በእኔ ሕይወት ውስጥ ቦታ አለህ” ማለት ሲሆን ይህም አብሮነትን የበለጠ ከፍ ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ አለው። ወዳጅነትን ያጠነክራል፣ አብሮነትን ያጎለብታል፤ በተለይም በማህበረሰቡ ዘንድ መከባበርና መደጋገፍ እንዲኖር የሚያደርግና ይበልጥም የአንድን ማህበረሰብ የጋራ እሴት     ወይም (Social capital) የማጠናከር እና የማሳደግ አቅም እንዳለውም ገልፀዋል፡፡

አክለውም ስጦታዎች የማህበረሰቡን መስተጋብር የሚያበለፅጉ እና አብሮ ለመኖርም ትልቅ ምሶሶ የሚሆኑ ናቸው። በተለይም ስጦታ ከቁስ በላይ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ “የስጦታ ፈረስ ጥርሱ አይታይም” እንዲሉ ከስጦታው ባሻገር ያለውን መተሳሰብ፣ አክብሮት እና ፍቅርን መመልከት እንደሚገባም ጉተማ ኢማና (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡

ስጦታ ኃይማኖታዊ አሊያም መንፈሳዊ ትርጓሜው መዘንጋት የለበትም፡፡ በመሆኑም       በሰጭና በተቀባዩ መካከል ያለው ግንኙነት ሚዛኑን መጠበቅ አለበት፡፡ በተለይ ስጦታው     አቅም ለሌላቸው፣ ችግርና ስቃይ ውስጥ ላሉ መሆን ይኖርበታል። ስጦታ የሚሰጠው ‘በሰጠሁት ልክ ይመልሳል’ ለምንለው ሳይሆን ልክ በአዲስ አበባና በአንዳንድ አካባቢዎች ከቅርብ አመታት ወዲህ እንደተጀመረው የማዕድ ማጋራትን በመሳሰሉ ተግባራት ችግረኞችን በመርዳት፣ እርስ በርስ በመጠያየቅ፣ አካባቢን በማፅዳትና መሰል ከቁስ ባሻገር ትርጉም ባላቸው ስጦታዎች ወይም በጎ ተግባራት ላይ ማተኮር እንደሚገባም መክረዋል፡፡

በተለይም ይላሉ ጉተማ (ዶ/ር) ከቅርብ አመታት ወዲህ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት የገናን በዓል በመሳሰሉ ወቅቶች ማዕድ የማጋራት፣  ችግረኞችን የመጠየቅና መደገፍ እንቅስቃሴ ይታያል፡፡ ይህም የማህበረሰቡን ትስስርና መስተጋብር የበለጠ የሚያጎለብት እንደ ሀገርም ትልቅ አቅምን የሚፈጥር ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህ ተግባራት ወደ እያንዳንዱ ግለሰብ የበለጠ እንዲወርዱ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩልም ስጦታን ለሌላቸው መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን ስጦታው ሚዛን የደፋ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም ስለስጦታ ስናስብ ወይም ስናስተምር ይህንን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይገባልም ብለዋል፡፡

የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ሶፎኒያስ ፍሰሃም፣ ጉተማ (ዶ/ር) ስለ ስጦታ በተለይም ለሌላቸው መስጠትን ከስጦታው ነገር በላይ ያለውን ማህበረሰባዊ አሊያም ሀገራዊ ፋይዳን አስመልክቶ የገለፁትን ሀሳብ ይጋራሉ፡፡ እንደ አቶ ሶፎኒያስ ገለፃ ኢትዮጵያውያን ስጦታ የመሰጣጠትም ሆነ እርስ በእርስ የመደጋገፍ ባህል ያላቸው መሆኑን አስታውሰው፣ በአመዛኙ ግን በገና ሰሞን የሚደረገው ስጦታ የመሰጣጠት ልማድ በምዕራቡ ዓለም በብዛት የተለመደ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

እንደ ማህበረሰብ ከሌላው ዓለም መልካም ነገሮችን መውሰዳችን ጥሩ ቢሆንም ከኢትዮጵያውያን ባህል ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ያስፈልጋል። ሁሉም ነገር እኛን ሲመስል ውጤቱ ዘላቂ እና ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ስጦታ በምንሰጥበት ወቅት በትክክል ለተቸገሩት እና አቅም ለሌላቸው መሆን እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ሀገርም ሆነ እንደ አዲስ አበባ ከተማ በበዓል ሰሞን እና መሰል ወቅቶች ማዕድ ማጋራት እና የተለያዩ ስጦታዎችን ለችግረኞች የመስጠትና የመጠያየቅ ሁኔታ በመንግስትም ሆነ በአንዳንድ ግለሰቦች እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህም ሊበረታታ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡

አንዱ ለሌላው ስጦታ በሚሰጥበት ጊዜ እርስ በርስ ያለው መተሳሰብ ይጎለብታል። እንዲህ አይነት ድርጊቶች ከፍ እያሉ በመጡ ቁጥር እንደ ማህበረሰብ ያለንና የነበረን መልካም እሴት እንዲጠበቅ፣ እንዲያድግና እንደ ሀገር ትስስሩ የጠነከረ ማህበረሰብ እንዲኖረን ያግዛልም ብለዋል አቶ ሶፎኒያስ፡፡

አክለውም በኃይማኖታዊ እሳቤውም ሆነ በማህበራዊ መስተጋብራችን የገና በዓል ስጦታ ከመሰጣጠት ጋር ይያያዛል፤ በአዲስ አበባም በግለሰብ ደረጃ ያለው ለሌለው አካፍሎ በዓሉን በደስታ ማሳለፍ የተለመደ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ማዕድ ማጋራት ባህል እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህም የአንድን ማህበረሰብ ሁለንተናዊ መስተጋብር ጤናማ በሆነ መልኩ ለማስቀጠል ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡

በተለይም በበዓል ሰሞን አቅም እና ጠያቂ የሌላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ማስታወስ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እንዲህ አይነት የህብረተሰብ ክፍሎች በችግር ውስጥ ያሉ በመሆናቸው በዓሉን ተደስተው እንዲያሳልፉ በምናደርግበት ወቅት ተስፋቸው ይለመልማል፡፡ ‘ለካ እኛንም የሚያስታውሰን አለ’ የሚል ስሜትን ስለሚፈጥርባቸው ስለ ነገ የተሻለ ነገርን እንዲያስቡ፣ ለለውጥ እንዲተጉና በማህበራዊ ህይወታቸውም እንዲኮሩ ስለሚያነሳሳቸው ይህን መሰል የመጠያየቅና የመደጋገፍ ባህል ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያደርግ እንደሚገባውም ጠቁመዋል፡፡

ባሳለፍነው ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለሃብቶችንና በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ለ263 ሺህ ወገኖች ማዕድ ማጋራቱ ይታወሳል፡፡ በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ማዕድ ማጋራት መደጋገፍን፣ አንድነትንና መተሳሰብን የሚያጎላ መልካም እሴት ስለመሆኑ ተናግረዋል። የከተማ አስተዳደሩ ይህን መልካም እሴት በማስቀጠል ረገድ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለፁት ከንቲባዋ፣ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ዜጎች በዘላቂነት ራሳቸውን የሚችሉበት አማራጮችን ማስፋት ዋነኛ ጉዳይ እንደሆነም መግለፃቸው አይዘነጋም፡፡

በርግጥም ከተማ አስተዳደሩ በበዓል ወቅት ከሚያደርጋቸው ማዕድ ከማጋራት ባሻገር የሆኑ በርካታ በጎ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ርሃብን ከማስታገስ ወደ ተመጣጠነ ምግብ የተሸጋገረውን የተማሪዎች ምገባን፣ በመዲናዋ ምንም አይነት ገቢ የሌላቸው አቅመ ደካማዜጎች ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ የሚመገቡባቸውን የምገባ ማዕከላት እና ሌሎቹንም በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2017 ዓ.ም አዲስ ዓመትን አስመልክቶ ባሳለፍነው መስከረም ወር ላይ በቤተ መንግሥት ለአቅመ ደካሞች ማዕድ አጋርተው ነበር፡፡ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክታቸው ማዕድ ማጋራት የሀገር ወዳድነት ምልክት፤ የወዳጅነት ውብ ማስታወሻ ነው። ማዕድ ማጋራት አንጡራ ባህላችን ነው። ካለን ላይ እናጋራ፤ ደስታን እንጋራ፣ እርስ በርሳችን እንደጋገፍ፤ በዓሉን በኀብረት ካለችን ለሌለው እያካፈልን ልባችንን እና ነፍሳችንን የሚመግቡ ትውስታዎችን በመፍጠር እናሳልፍ ማለታቸው ይታወሳል።

የማህበራዊ ሳይንስ እና የኃይማኖት ሊቃውንት መስጠት አንድም በደስታ ብርሃን     የሚያጥለቀልቅ፣ ከሕይወት ፍፃሜም በላይ ሰማየ ሰማያትን አብሮ የሚዘልቅ የማይዳሰስ እሴትን በልቦና ውቅር ውስጥ የሚያስቀምጥ ሲሆን፣ በሌላ በኩልም ለምድራዊ ኑሯችን ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አብሮነትን እና መተሳሰብን በህብረታችን መሐል የማነፅ ትልቅ ኃይል እንዳለው ይናገራሉ፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review