የአውሮፓ ዋንጫ ጉዞ ሲቃኝ

You are currently viewing የአውሮፓ ዋንጫ ጉዞ ሲቃኝ

የዴይሊ ሜይል ፀሐፊው ኪራን ሊንች በአውሮፓ ዋንጫው ተመልክቶት ያስገረመው ጉዳይ እርሱን ብቻ አስደንቆት ያበቃ አልነበረም። ሩማኒያውያን ያሳዩት ስፖርታዊ ጨዋነት፣ ስነ ስርዓት፣ መከባበርና ጨዋ ተሸናፊነትን ለስፖርት ቤተሰቡ አስተምረዋል፡፡ የእግር ኳስ ቤተሰቡን ቀልብ የሳበና ለብዙዎች ትምህርት የሰጠ ተግባር ፈጽመው የበዛ አድናቆት ተችሯቸዋል። በአውሮፓ ዋንጫ የኔዘርላንድስ ሽንፈትን ተከትሎ ከውድድሩ የተሰናበቱት የቀድሞ እግር ኳስ ኮከብ ጆርጅ ሀጂ ሀገር ሮማኒያውያን መጫወቻ ሜዳውን ለቅቀው የወጡበት ጨዋነት ሳያንስ መልበሻ ክፍላቸውን ጥለው ወደ ሀገራቸው የተመለሱበት መንገድ ደግሞ ብዙዎችን አስገርሟል፤ ትምህርትም ሰጥቷል፡፡

በዛሬው ዕለት መቋጫውን በሚያገኘው 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ላይ ከምድቡ በጥሩ ብቃት ያለፈው የሮማኒያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ጥሎ ማለፉ ከተሸጋገረ በኋላ በኔዘርላንድ 3-0 ተሸንፎ ከውድድር ውጪ ሆኗል። ጨዋታውም ሲያልቅ ተጫዋቾቹ ጊዜ ወስደው ከደጋፊዎቻቸው ጋር ተመሰጋግነው ሜዳ ለቅቀው ወጥተዋል። የመልበሻ ክፍላቸውንም አጽድተው ለቅቀው ሲወጡም ደብዳቤ አስቀምጠው ነው፡፡

በደብዳቤው “በውድድሩ ወቅት ለነበረን ቆይታ ሁሉ እናመሰግናለን፡፡ ለተደረገልን አቀባበል ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው፡፡ በዚህ አውሮፓውያን ሁሉ በአንድነት በሚገኙበት መድረክ ላይ በመገኘታችንም ደስተኞች ነን፡፡” በማለት ለአዘጋጇ ሀገር ጀርመን መልዕክት አስተላልፈው ነበር የሄዱት። ይህንን የተመለከተው የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበርም ሽንፈታቸውን በክብር ለተቀበሉት ሩማንያውያንን ጨዋ እንግዶች ሲል አሞካሽቷቸዋል፡፡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡናና ወላይታ ዲቻ ጨዋታ ላይ የተከሰተውንና ብዙዎችን ያሳዘነውን ተግባር በንጽጽር እያሰብን ወደ አውሮፓ ዋንጫው ክራሞት  እንዝለቅ፡፡

በጀርመን ለአንድ ወር ገዳማ ሲከናወን ቆይቶ በዛሬው ዕለት መቋጫውን የሚያገኘው የ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ የብዙ እግር ኳስ አፍቃሪያን የዐይን ማረፊያ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ታላላቅ ስፖርተኞች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ከተለያዩ ሀገራት ውድድሩን ለመከታተል ጀመርን የተገኙ የእግር ኳስ ቤተሰቦችም አስተያየት የሚነግረን ይህንኑ ነው፡፡ ውድድሩን ለመከታተል ለቀናት የከተሙት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደጋፊዎች በተለይም አንደ ኔዘርላንድስ፣ ሮማኒያና ክሮሺያ ያሉ ደጋፊዎች ያሳዩት የነበረው ድጋፍ ለአውሮፓ ዋንጫው ድምቀትና አስገራሚ ድባብ ፈጥረውለታል፡፡ የትውልደ አፍሪካውያን ተጫዋቾች የሜዳ ላይ ተጽዕኖም የመገናኛ ብዙሃኑን የፊት ገጽ ዋና ጉዳይ ሆኖም ቆይቷል፡፡

ትውልደ አፍሪካውያን የደመቁበት ውድድር

የዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ ከምንጊዜውም በላይ የደመቀ እና የባሕል ስብጥር የበዛበት እንዲሆን ካደረጉት ጉዳዮች መካከል የትውልደ አፍሪካውያን ተሳትፎ ተጽዕኖ ፈጣሪነት መጨመር ሌላኛው ምክንያት ነበር። ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀሉትም ይሁኑ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የሚሸጋገሩ ብሔራዊ ቡድኖች ውጤታማ ከሆኑባቸው ምክንያቶች አንዱ የትውልደ አፍሪካዊያን ተጫዋቾች ውጤታማነት  ስለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡

በርካታ ጥቋቁር ከዋክብት፣ የዘር ሐረጋቸው ከሚመዘዝባት፣ ማንነታቸው ከሚቀዳባት አፍሪካ ርቀው በስደት ለተወለዱበት ሀገር የሚጫወቱ በርካቶች ናቸው፡፡ በአብዛኛው በስደት አልፎ አልፎም ደግሞ በአፍሪካ ያለው የስፖርቱ የተመቸ ከባቢ ያለመኖር ከእግር ኳስ አስተዳደር ችግር ጋር ተደምሮ በርካታ አዳጊዎች ወደ ተለያዩ ሀገራት ይሰደዳሉ፤ በተለይም ወደ አውሮፓ፡፡ ኬቪን ዳንሶ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። የ25 ዓመቱ ተከላካይ ለትውልድ አገሩ ኦስትሪያ መከታ ነበር። ኦስትሪያ ወደ ዙር 16 ብትደርስም በቱርክ ተሸንፋ ከውድድር ውጪ ሆናለች። ዳንሶ ምንም እንኳን ኦስትሪያ ይወለድ እንጂ ከ6 ዓመቱ ጀምሮ ከጋናውያን ቤተሰቦቹ ጋር የኖረው እንግሊዝ ውስጥ ነው። የእግር ኳስ ክህሎቱን ያካበተውም በሬዲንግ እና ኤም.ኬ ዶንስ አካዳሚዎች ነው። ለፈረንሳይ ሊግ 1 ክለብ ላንስ የሚጫወተው ዳንሶ “ኦስትሪያን ቤቴ፤ ጋናን ደግሞ የአያቶቼ መገኛ ብዬ መጥራት በመቻሌ እጅግ ዕድለኛ ነኝ” ሲል ለቢቢሲ ተናገሯል።

ስፔን በ2000ዎቹ በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ መድረክ የበላይነቷን ያሳየችው ረጋ ብሎ ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት ነበር። ነገር ግን አሁን ይህ የተቀየረ ይመስላል። የስፔንን እግር ኳስ በክንፍ በኩል እየመሩ ያሉት ደግሞ ወጣቶቹ ኒኮ ዊሊያምስ እና ላሚን ያማል ላ ሮሀ ናቸው። ኒኮ ዊሊያምስ ጋናዊ ደም ያለው ሲሆን፣ ላሚን ያማል ደግሞ ከሞሮኮ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ የሚመዘዝ የዘር ግንድ አለው።

ጋናዊያኑ የተሻለ ኑሮን ፍለጋ የሰሃራ በረሃን አቋርጠው ስፔን መኖር ከጀመሩ በኋላ ነው ኒኮ እና ኢናኪን የወለዱት። ኢናኮ ከኒኮ በተለየ የአራት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ለሆነችው ጋና መጫወትን መርጧል። ኢናኪ ከጋና ብሔራዊ ቡድን ጋር እያደረገ ያለው ጉዞ ይህን ያህል ስኬታማ ባይሆንም፣ ኒኮ ግን ከስፔን ብሔራዊ ቡድን ጋር የተሳካ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። በዙር 16 አገሩ ስፔን ጆርጂያን 4-1 ስትረታ የመጀመሪያ የአውሮፓ ዋንጫ ጎሉን ያስቆጠረው ኒኮ ከዚህ ጨዋታ በፊት ያሳየው ብቃት የወደፊት የቡድኑ ተስፋ መሆኑን ያስመሰከረ ነው። በተለይ ስፔን ጣሊያንን ስታሸንፍ ጎልቶ መውጣት ችሏል።

ሌላኛው ለስፔን ብሔራዊ ቡድን እየተጫወተ የሚገኘው የ16 ዓመቱ ያማል ገና በዚህ ዕድሜው አስደናቂ ተጫዋች መሆኑ ብዙዎችን እያስገረመ ነው። በተለይ የውሳኔ ብቃቱን ብዙዎች ያወድሱለታል። የባርሴሎናው አዳጊ በጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ እያሳየ ያለውን ድንቅ ብቃት በ16 ዓመታቸው ማሳካት የቻሉ በጣም ጥቂት ናቸው። ሞሮኮ ልክ እንደ አሽራፍ ሐኪሚ እና ብራሒም ዲያዝ ሁሉ ያማልን ከስፔን ነጥቃ የራሷ ለማድረግ ያደረገችው ጥረት አልተሳካላትም።

የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ አዘጋጅ አገር ጀመርን ከስፔን ቀጥሎ ጠንካራ ቡድን ይዛ የቀረበች ቡድን ነበረች፡፡ ከዴንማርክ የገጠማትን ፈተና አልፋ ወደ ሩብ ፍፃሜው የተሸጋገረችው ጀርመን ለዋንጫው ግምት ከተሰጣቸው መካከል ብትሆንም በስፔን ተሸንፋ የዋንጫ ግስጋሴዋ ተገትቷል። ምንም እንኳን ካይ ሀቨርትዝን አጥቂ አድርጎ መጠቀም እንዲሁም ፍሎሪያን ቪርትዝን ክንፍ ላይ ማሰለፍ አዋጭ አይደለም የሚሉ ትችቶች ቢሰሙም ወጣቱ ጀማል ሙሲያላ የጀመርን ተስፋ መሆኑን አስመስክሯል። የትኛውን ብሔራዊ ቡድን ወክዬ ልጫወት? የሚለው ውሳኔ ቀላል እንዳልነበረ የ21 ዓመቱ ሙሲያላ ይናገራል። “ከናይጄሪያም ሆነ ከጀመርን ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ንግግር አድርጌያለሁ። ያው ውሳኔው የእኔ እንደሆነ እና የትኛው ይመቸኛል የሚለው ሐሳብ መሠረት ያደረገ እንደሆነ አውቃለሁ። ለዚህ ነው ጀመርንን የመረጥኩት” ይላል።

የትውልድ ቦታው ቶጎ የሆነው ሆላንዳዊው አጥቂ ኮዲ ጋክፖ እና ትውልደ ጋናዊ ለቤልጂየም እየተጫወተ የሚገኘው ጀርሚ ዶኩ ጨምሮ በአውሮፓ ዋንጫው እስከ 40 የሚደርሱ ትውልደ አፍሪካውያን እየተሳተፉ ስለመሆኑ የቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ መረጃ ያሳያል።

በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ይህን መረጃ እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ በ48 ጨዋታዎች 114 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን፣ ይህም በአንድ ጨዋታ በአማካይ 2 ነጥብ 25 ጎሎች ተቆጥረዋል እንደማለት ነው። በእርግጥ ይህ አሃዝ ከ2020 የአውሮፓ ዋንጫ ጋር ሲነጻጸር በቁጥር ያነሳ ነው። ከአራት ዓመት በፊት በተሰናዳው ውድድር ላይ በአማካኝ 2 ነጥብ 7 ግቦች ይቆጠሩ ነበር፡፡ በ51 ጨዋታዎች 142 ጎሎች ተቆጥረዋል፡፡

ለዚህም እንደ ጋሪ ሊኒከር ያሉ የቀድሞ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድ ተጫዋች አስተያየት ከሆነ ይህ የሆነበት ምክንያት ቡድኖቹ የተመጣጠነ ደረጃ ላይ መድረሳቸውና የጥቂት ብሔራዊ ቡድኖች የበላይነት በማክተሙ ነው፡፡ በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው ጆርጂያ፣ ቱርክ፣ ኦስትሪያን የመሳሰሉ ብሔራዊ ቡድኖችም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ መሆን የሚችሉ ናቸው፡፡ በዓለም የእግር ኳስ ደረጃ ስድስተኛ ላይ የምትገኘው ፖርቹጋል እጅ የሰጠችው 74ኛ ደረጃ ላይ ለምትገኘው ጆርጂያ መሆኑ ደግሞ የቀድሞው ተጫዋች ጋሪ ሊኒከርን መከራከሪያ የሚያጠናክር ሆኖ እናገኘዋለን።

የአውሮፓ ዋንጫው ከ74 ሺህ በላይ ተመልካቾችን ማስተናገድ በሚችለው የበርሊን ኦሎምፒክ ስታዲየም በስፔን እና በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል በዛሬው ዕለት ፍጻሜውን ያገኛል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review