AMN – መስከረም 23/2017 ዓ.ም
የአጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ልዩነቶችን ይፈታል ያልናቸውን ሀሳቦች በነጻነት የገለጽንበት ነው ሲሉ የአፋር ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡
ከመስከረም 21 ቀን ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብና ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊ ተወካዮች መረጣ ሂደት በሰመራ ከተማ ከ9 የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ከ800 በላይ ተሳታፊዎች እየተመካከሩ ቀጥለዋል።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱም ግልጽና አሳታፊ የሆኑ ምክክሮችን ማድረጋቸውን ነው ለኤኤም ኤን አስተያየታቸውን የሰጡ የተለያዩ ማህበረሰብ ወኪሎች የተናገሩት።
ከእነዚህም ውስጥ የተፈናቃይ ፣የጎሳ መሪዎችና አርብቶ አደር ወኪሎች ይገኙበታል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች በእኩልነት በማሳተፍ የጀመረው የምክክር ምዕራፍ እንደ ሀገር ብሎም እንደ ክልል እያጋጠሙ ላሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ይሰጣል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
የአጀንዳ የማሰባሰብና ለምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ወኪሎችን የመምረጥ ሂደቱም በግልጽና በነጻነት ሀሳባቸውን እያነሱ መሆናቸውንም ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት።
በተለይም ተፈናቃይ የማህበረሰብ ክፍሎች የምክክሩ ተሳታፊ መሆናቸው ለችግሮች እልባት እንደሚኖር ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ለመፈናቀል የዳረገን ከውይይት ይልቅ ግጭትና ጦርነትን የመረጡ ሀይሎች በመኖራቸው ነው ያሉት ተወካዮቹ ለኢትዮጵያ ችግር መፍቻው ቁልፉ ምክክርና ውይይት ብቻ ነው ብለዋል።
በመሆኑም በአጀንዳ የማሰባሰብ ምክክራችን ለሀገር ይጠቅማል ብሄራዊ መግባባትን ያመጣል ያልናቸውን ሀሳቦች አንስተናል ብለዋል።
የማህበረሰብ ወኪሎች የቡድን ውይይቶችን ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ ለዋናው የምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ስድስት ወኪሎችንም መርጠዋል።
በፍቃዱ መለሰ