የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዘርፍ አፈጻጸም እጅግ አመርቂ መሆኑን ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሀገራዊ የዘጠኝ ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጻምን ተከትሎ የዘርፍ ውይይት ከሚኒስቴር መስረያ ቤቱና ከተጠሪ ተቋማት ሰራተኞችና አመራሮች ጋር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በተገኙበት አካሂደናል ብለዋል፡፡
በውይይቱም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አፈጻጸም እጅግ አመርቂ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም የአለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድርን እውን ለማድረግ በ5ኛው የስራ ላይ ቡድን ስብሰባ አስተማማኝ ስራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠና ስምምነትን የሙከራ ንግድ ለማስጀመርም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ሲሉም አክለዋል፡፡
ሚኒስትሩ፣ በቀጣይ ሶስት ወራትም በበጀት አመቱ የታቀዱ ተግባራትን በከፍተኛ ርብርብና በላቀ ውጤት እናጠናቅቃለን ብለዋል።