“የአፍሪካ አዳራሽ መታደሱ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ጉዳዮች አስፈላጊ ሀገር መሆኗን የሚያስረግጥ ነው”

የታሪክ ተመራማሪ አየለ በከሬ (ፕ/ር)

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ረጅም የመንግስትነት ታሪክ ካላቸው ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ በተጋድሎ ነፃነቷን አስጠብቃ በመኖር፣ በጭቆናና ቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ የሚገኙ የአፍሪካና በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ህዝቦች ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ መነሳሳት በመፍጠር የነፃነት ቀንዲል ተደርጋ ትታያለች፡፡

ለአስራ አራት ዓመታት ያህል በአሜሪካ ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናትና ምርምር ማዕከል የአፍሪካ ታሪክ፣ ስልጣኔና ባህል በሀገር ውስጥ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ጭምር ያስተማሩት የታሪክ ተመራማሪው አየለ በከሬ (ፕ/ር) እንደሚሉት፣ በተለይ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት በማዋል ልትገዛት የመጣችውን ጣሊያንን በማንበርከክ ነፃነቷን ያስቀጠለችበት የዓድዋ ድል፣ በአፍሪካ የፀረ ቅኝ ግዛት ትግልን በማቀጣጠል ትልቅ ቦታ እንዲኖራት አድርጓል። ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስጠብቃ በመቀጠልና ቅኝ ግዛትን በመታገል በምታደርገው ትግል በፈረንጆች 1923 የዓለም መንግስታት ማህበርን (ሊግ ኦፍ ኔሽን) ተቀላቅላለች፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ እ.ኤ.አ በ1945 በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሲመሰረት ከመስራች አባል ሀገራት መካከል አንዷ መሆን ችላለች፡፡

የታደሰውን ታሪካዊ የአፍሪካ አዳራሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፣ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እና ሌሎች የሥራ ሃላፊዎች በመረቁበት ወቅት

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሲመሰረት በስሩ ከተቋቋሙ ስድስት ዋና ዋና ተቋማት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ካውንስል አንዱ ነው፡፡ ካውንስሉ በየአህጉሩ ክልላዊ አደረጃጀቶችን የመሰረተ ሲሆን፣ በ1958 ባደረገው ጉባኤ በአፍሪካ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ልማትን ለማፋጠን፣ የአፍሪካውያንን የእርስ በእርስ ትስስርና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን በማሳደግ ልማትን ለማፋጠን የሚሰራ “የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን” የተሰኘው እንደተመሰረተ በኮሚሽኑ ገፀ ድር ላይ የወጣው መረጃ ያሳያል፡፡ 

የታሪክ ተመራማሪው አየለ (ፕ/ር) እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስጠብቃ በመቀጠልና በዓለም አቀፍ መድረክ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ ባደረገችው ያላሰለሰ ትግል የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና መቀመጫውን በኢትዮጵያ ዋና ከተማ በአዲስ አበባ ሊያደርግ ችሏል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ገፀ ድር ላይ የወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ በወቅቱ በአዲስ አበባ አለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ማስተናገድ የሚችል አዳራሽ ወይም አቅም ስላልነበራት የያኔው የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ለድርጅቱ ጽህፈት ቤትና ስብሰባ አገልግሎት የሚውል ህንጻ በአጭር ጊዜ እንዲገነባ አዘዙ፡፡ የህንፃ ግንባታው ንድፍም በጣሊያናዊው አርክቴክት አርቱር ሜዝዴሚ ተሰርቶ፣ በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ተገንብቶ በፈረንጆች አቆጣጠር 1961 በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ በይፋ ተመርቋል።

የአፍሪካ አዳራሽ ከምርቃት በኋላ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የተለያዩ ጉባኤዎችን አስተናግዷል። አዳራሹን በአፍሪካ ታሪክ ልዩ ምዕራፍ እንዲኖረው ያደረገው በፈረንጆቹ አቆጣጠር 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ሲመሰረት በጊዜው ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡ 32 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የድርጅቱን መመስረቻ ስምምነት (ቻርተር) የተፈራረሙበት መሆኑ ነው፡፡ የቻርተሩ መፈረም የአፍሪካውያንን አንድነትን በማጠናከር በድህረ ቅኝ ግዛት ታሪክና በፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ውስጥ ትልቅ ስኬት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

የታሪክ ተመራማሪው አየለ (ፕ/ር) እንደሚገልፁት፤ “ፓን” አፍሪካኒዝም አፍሪካውያን የጋራ የሰቆቃ ታሪክ የሚጋሩ፣ የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው የተሳሰረ እንደመሆኑ፣ በአንድነት በመቆም ጥቅማቸውን ማስከበር ይችላሉ የሚል እሳቤ ነው፡፡ ወደ አንድነት እንዲመጡ በተለይም “ፖለቲካዊ ውህደት በማድረግ አንድ አፍሪካን እንፍጠር” እና “መጀመሪያ ራሳችንን እንደ አገር ቆመን በኢኮኖሚ ከተጠናከርን በኋላ ወደ ውህደት እንሄዳለን” የሚሉ የካዛብላንካ እና የሞኖሮቪያ ቡድን መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ ወደ ስምምነት እንዲመጡ በማድረግ የኢትዮጵያ ድጋፍ ትልቅ ነበር፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ሲመሰረት የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ተቋማዊ ቅርፅ መያዝ መቻሉን ያነሳሉ፡፡

የአዳራሹ እድሳት

በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘው የአፍሪካ አዳራሽ ከተገነባ ከ61 ዓመት በላይ እድሜ አስቆጥሯል፡፡ ከእድሜው አኳያ እድሳት እንደሚያስፈልገው ታውቆ ፋይናንስ ለማፈላለግ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ እንደነበር የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በገፀ- ድሩ ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተመሰረተበት 50ኛ ዓመት በዓል ሲከበርም በአፍሪካ ታሪክ ትልቅ ስፍራ ያለው የአፍሪካ አዳራሽን ለማደስ የኢትዮጵያ መንግስት፣ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋምና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በጋራ በመሆን እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡

በፈረንጆቹ በ2014 እድሳቱን ለማከናወን የአዋጭነት ጥናትና ዲዛይን እንዲሰራ ከተደረገ ከአንድ ዓመት በኋላ የተባበሩት መንግስታት 70ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያከናውን በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ክትትል እድሳቱ እንዲከናወን ተፈቀደ፡፡ ህንፃው ሲታደስም የኢትዮጵያ መንግስት በዓይነት መልክ ለቋሚ ኤግዚቢሽን ማሳያ ግንባታና ኤግዚቢሽኑን ለመጎብኘት የሚመጡ ሰዎች የተሽከርካሪ ማቆሚያ የሚሆን 3 ሺህ 100 ካሬ ሜትር ቦታ መስጠቱን ከአንድ ወር በፊት የእድሳቱን ሂደት በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ የሰጡት የአፍሪካ አዳራሽ ፕሮጀክት የሲቪል እና አርክቴክቸራል ሥራዎች ሱፐርቫይዘር ኢንጂኒየር ጌታቸው አርዓያ ተናግረዋል፡፡

የእድሳቱ ዓላማም ህንፃውን በማዘመን፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ምቹ አገልግሎት መስጠት እንዲችል፣ የአፍሪካ ታሪክና ቅርስ ጉልህ መዘክርና ልዩ ምልክት ሆኖ ለመጪው ትውልድ እንዲሸጋገር ለማድረግ ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በመደበው 57 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ዘመኑን በሚመጥን መልኩ የኮንፈረንስ ማዕከልና ሙዚየም ሆኖ ማገልገል እንዲችል ተደርጎ እድሳት ተደርጎለትም ከሰሞኑ በይፋ ተመርቋል፡፡

አዳራሹ ምን ይዟል?

የአፍሪካ አዳራሽ ከዋናው አዳራሽና የተለያየ አገልግሎት ከሚሰጡ ክፍሎች በተጨማሪ ሰባት የሚሆኑ የአፍሪካን መልኮች የሚገልፁ የረቀቀ የአሳሳል ጥበብ የሚታይባቸው ስዕሎችን በውስጡ ይዟል፡፡ ከእነዚህ መካከል በ150 ስኩዌር ሜትር ስፋት በአዳራሹ መስኮቶች ላይ  ያረፉ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የተጠበቡባቸው ስዕሎች ይገኛሉ፡፡ “ቶታል ሊብሬሽን ኦፍ አፍሪካ” የሚል ስያሜ ያላቸው የመስታወት ስዕሎች የአፍሪካን የትናንት ጭቆና፣ የዛሬ ፈተናዎችና የወደፊት መፃኢ ተስፋ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ እንደ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ፣ ጆሞ ኬንያታ፣ ክዋሜ ንክሩማህ ያሉ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረቻ ቻርተርን የፈረሙ 32 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችን የያዘ ስዕል፣ ከአፍሪካ ህብረት አባላት የተገኙ የተለያዩ ጥበባዊ ስራዎች ይገኛሉ፡፡ 

ህንፃው የጎብኚዎች ማዕከል፣ ቋሚ የኢግዚቢሽን ማሳያ ማዕከል እና የተለያዩ ዘመናዊ የኮንፈረንስ ስርዓት ግብአቶች አሟልቶ የተገነባ ነው፡፡ የጎብኚዎች ማዕከል ድርጅቱን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች የአፍሪካን ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ታሪክ የሚማሩበት እንዲሆን ታስቦ የተሰራ ነው፡፡

እድሳቱ የአዳራሹን ታሪካዊ፣ ኪነ ህንፃና ጥበባዊ ይዘቶችን በጠበቀ መልኩ የተከናወነ መሆኑ የፕሮጀክቱ ትልቅ ስኬት መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል። የራሷን መዳረሻ በራሷ ለማበጀት ስትታገል ለነበረው አፍሪካ፣ የአህጉሪቱን ነፍስያ ታሪክ ለማጥናት ልዩ ቦታ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

የታደሰውን ታሪካዊ አዳራሽ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መኸመትን ጨምሮ ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል። በምርቃቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ “ይህ ስፍራ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት የተወለደበት፣ የአህጉራችን ጉዞና አቅጣጫ የቀየሩ ወሳኝ ውሳኔዎች የተወሰኑበት ህያው ማስረጃ ነው፡፡ ልዩ የሆነውን የአፍሪካ አዳራሽ ደረጃቸውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የኪነ ህንፃና ጥበባዊ ስራዎችን በጠበቀ መልኩ የእድሳት ስራው መከናወኑም የፓን አፍሪካኒዝም ታሪክ እና የጋራ የወደፊት ተስፋችንን ለመጠበቅ ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ መንግስት የተገነባው አዳራሽ የአንድነት፣ የተስፋና ፈተና ተቋቁሙ የማለፍ ብርታት ምልክት ነው፡፡” ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው፤ “ይኼ አዳራሽ አፍሪካውያን ተሰባስበው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑን የአፍሪካ ህብረት ህይወት የዘሩበት ስፍራ ነው፡፡ የታደሰው ህንፃ የአፍሪካውያን የታደሰ ተስፋና አንድነት ተምሳሌት ነው፡፡  የአፍሪካን ትናንት  እና  ነገየሚያገናኝ ድልድይ፣ የጋራ ፈተናዎችና ስኬቶች የሚዘከሩበት፣ የጋራ የወደፊት ተስፋ የሚሰነቅበት ነው፡፡ እድሳቱም የታላቁን አህጉር የታላቅነት ታሪክ ይዞ ዘመኑ የደረሰበትን የኪነ ህንጻ ጥበብ ደረጃ በጠበቀ መልኩ የተከናወነ ነው” ብለዋል፡፡ 

አፍሪካ የተስፋ ምድር ናት፡፡ ነገር ግን የታሪክ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭትና ድህነት ፈተናዎች ሆነው ቀጥለዋል ያሉት ዋና ፀሀፊው፤ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ቆራጥ እርምጃ እና በአዲስ መንፈስ መተባበር እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሀፊ ክላቨር ጌታቴ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ አዳራሽ ህንፃ ተገንብቶ የተመረቀበት የፈረንጆቹ 1961 የአፍሪካ ህዳሴ መነሻ እንደሆነና የኢትዮጵያ መንግስት ህንፃውን በመገንባት ያደረገው ድጋፍ ልዩ ምስጋና እንደሚገባው አንስተዋል። ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካኒዝም ትግል ያላት አሻራና የበለፀገ ታሪክ የሚያሳየው የአፍሪካ አዳራሽ ሀገሪቱ ከቱሪዝም ያላትን ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችል ትልቅ እድል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የታሪክ ተመራማሪው አየለ (ፕ/ር) እንደገለፁት፤ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና መቀመጫው በአዲስ አበባ መሆኑ፣ ታሪካዊ የአፍሪካ አዳራሽ ህንፃ ትልቅ ወጪ ወጥቶበት እንዲታደስ መደረጉ በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ኢትዮጵያ አስፈላጊ ሀገር መሆኗን የሚያስረግጥ ነው፡፡ አንዳንድ የኢትዮጵያን ማደግ በበጎ በማይመለከቱ ወገኖች ዘንድ የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ ከኢትዮጵያ እንዲወጣ የሚከፈተውን የዘመቻ ሀሳብ ውድቅ የሚያደርግ፣ የኢትዮጵያን የአፍሪካና የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከልነት የሚያፀና ነው፡፡ የአፍሪካ አዳራሽ ጎልቶ እንዲወጣና እንዲታወቅ ያደረገው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተበት ስፍራ መሆኑና በኋላም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና መቀመጫ በአዲስ አበባ እንዲሆን መደረጉ ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ወደ አዲስ አበባ መጥተው አዳራሹን መመረቃቸውም፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የበለጠ አፍሪካን እንዲደግፍ ያደርጋል፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ መናኸሪያነቷንና በአፍሪካ ያላትን ቦታና ተፈላጊነት ያሳድጋል፡፡ በሁሉም መልክ የአዲስ አበባን ዓለም አቀፋዊ ከተማነት የሚያሳድግ ነው፡፡ አፍሪካን በሚመለከቱ ጉዳዮች ዋነኛ ቦታ እንዲኖራትም ያደርጋል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ አዳራሽ የአፍሪካ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ታሪክ የሚታወስበት፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ መድረክ የአፍሪካን ጉዳይ በማስቀደም እያደረገች ላለው ትግልና ጥረት መስታወት የሆነ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአፍሪካ ውስጥ የከፈተው የመጀመሪያው መሰብሰቢያ ስፋራ ነው፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review