የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ በዓላት በስኬት እንዲከበሩ የፀጥታ እና ደህንነት አካላት ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው ወደ ስራ ገብተዋል – ፌዴራል ፖሊስ

You are currently viewing የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ በዓላት በስኬት እንዲከበሩ የፀጥታ እና ደህንነት አካላት ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው ወደ ስራ ገብተዋል – ፌዴራል ፖሊስ

AMN – መስከረም 21/2017 ዓ.ም

የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የፀጥታና ደህንነት አካላት ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው ወደ ስራ መግባታቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ይህን ያስታወቀው የፀጥታና ደህንነት አካላት የመስቀል ደመራ በዓል በስኬት መጠናቀቁን አስመልክተው በዛሬው እለት ባደረጉት ግምገማ ላይ ነው።

የፀጥታና ደህንነት አካላት ባካሄዱት የተቀናጀ ኦፕሬሽን የመስቀል ደመራ በዓልን ለማደናቀፍ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብርና የፅንፈኛ ቡድን አባላትን እኩይ ዓላማ በአስተማማኝ ሁኔታ በማክሸፍ ከተለያዩ የጦር መሳሪያዎች፣ ቦንቦች እና የፀጥታ አካላት የደንብ ልብሶች ጋር በቁጥጥር ሥር አውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ በግምገማው ላይ አንስተው ህብረተሰቡ ላደረገው ከፍተኛ ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።

የመስቀል በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላምና በስኬት እንዲከበር የፀጥታና ደህንነት አካላት ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር የተቀናጀ ውጤታማ የፀጥታ ስራ መስራታቸውን ገልፀው መስከረም 25 እና 26 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ የሚከበሩት የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዓላት ባህላዊ ስርዓታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ በርካታ የፀጥታ ሀይል አሰማርቶ ወደ ስራ መገባቱን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

የኢሬቻ በዓል ከሚፈቅደው ባህላዊ ስርዓት ተቃራኒ የሆኑ ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎችና መልዕክቶችን ይዞ መገኘት ፈፅሞ የተከለከለ ሲሆን በዓሉን ለእኩይ ዓላማ ለመጠቀም የሚደረጉ ማንኛውም ዓይነት ሕገ-ወጥ ተግባራት በፍፁም ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን የፀጥታና ደህንነት አካላት አስታውቀው ይህንን በመተላለፍ በዓሉን ለማወክ በሚንቀሳቀስ ማንኛውም ግለሰብና ቡድን ላይ ጠንካራ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ መግለጻቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የፀጥታ አካላት በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ በርካታ አጋዥ የህብረተሰብ ክፍሎች በፀጥታው ሥራ ላይ እየተሳተፉ እንደሆነ አንስተው ኅብረተሰቡ ከፖሊስ የሚተላለፉ የክልከላ መልዕክቶችን በማክበር ፀጥታን የሚያደፈርሱ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲመለከት የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን (EFPApp) ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 በመጠቀም ጥቆማዎችን በፍጥነት በመስጠት ወይም መረጃውን በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች በአካል በማድረስ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review