የኢትዮጵያ ስታርታፕ ዲጂታል ፕላትፎርም ዘርፉን ለማሳደግ እና ኢኮኖሚውን የመደገፍ ፋይዳ አለው- ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር)

You are currently viewing የኢትዮጵያ ስታርታፕ ዲጂታል ፕላትፎርም ዘርፉን ለማሳደግ እና ኢኮኖሚውን የመደገፍ ፋይዳ አለው- ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር)

AMN – መጋቢት 2/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ስታርታፕ ዲጂታል ፕላትፎርም ዘርፉን ለማሳደግ እና ኢኮኖሚውን የመደገፍ ፋይዳ አለው ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኮሪያ ዓለም ዓቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ኮይካ) ጋር በመተባበር የስታርታፕ ዲጂታል አማራጭ ዲዛይን ምዕራፍ የተመለከተ አውደ ጥናት አካሄዷል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ፣ በኢትዮጵያ የኮሪያ ዓለም ዓቀፍ ተራድኦ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ያንግሺን ፓርክ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ማዕቀፉ የኢትዮጵያን የጀማሪ የስራ ፈጠራ (ስታርታፕ) ዘርፍ ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል ምቹ ስነ-ምህዳር መፍጠርን ያለመ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የስታርታፕ መድረክ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል ስነ-ምህዳር ለመገንባት እየሰራች እንደምትገኝ አመልክተዋል።

ስታርታፕ ፈጣን የሀገር ኢኮኖሚ ማበልፀጊያ ሞተር ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የኢትዮጵያ ስታርታፕ ዲጂታል ፕላትፎርም ዘርፉን ለማሳደግ እና ኢኮኖሚውን የመደገፍ ፋይዳ አለው ብለዋል።

መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ብዙ ሀብት ማፍራት የቻሉ ወጣቶች እና ዜጎች ተፈጥረዋል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።

በኢትዮጵያ የኮሪያ አለም ዓቀፍ ተራድኦ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ያንግሺን ፓርክ (ካይካ) ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በስታርታፕ ዘርፍ ላይ የምታደርገውን የስነ-ምህዳር ግንባታ ስኬታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አመልክተዋል።

ኮይካ ኢትዮጵያ በዘርፉ ለምታከናውናቸው ስራዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review