AMN-መስከረም 22/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተያዘው በጀት ዓመት አምስት አዳዲስ ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎች የሚኖሩት መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
አየር መንገዱ በየዓመቱ አዳዲስ መዳረሻዎችን በማስፋትና የአውሮፕላኖችን ቁጥር በመጨመር ዓለም አቀፍ አገልግሎቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።
የአፍሪካ አቪዬሽን መሪ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.አ.አ በራዕይ 2035 በዓመት 67 ሚሊየን መንገደኞችን በማጓጓዝ 25 ቢሊየን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ለማግኘትም እየሰራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አየር መንገዱ አምስት ተጨማሪ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ላይ ሥራ መጀመሩን አስታውሰዋል።
በ2017 በጀት ዓመትም አምስት አዳዲስ ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎች እንደሚኖሩት ገልፀዋል።
የበረራ መዳረሻዎች ከሚሆኑት መካከልም ሆላንድ አምስተርዳም፣ ላይቤሪያ ሞኖሮቪያ፣ ፖርት ሱዳንና ዳካ ባንግላዲሽ የሚገኙበት መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስካሁን ከአውስትራሊያ በስተቀር በሁሉም አህጉሮች የበረራ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አንስተው፤ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ወደ አውስትራሊያ ለመብረር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚገዛቸው አውሮፕላኖች በተጨማሪ በኪራይና ሌሎች አማራጮች ምቹና ሰፊ የበረራ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ላይ በ147 አውሮፕላኖች 139 ዓለም አቀፍና 22 የሀገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎች እንዳሉት ይታወቃል።