የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ ለስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎች መስፋፋት ላደረጉት አስተዋጽኦ እውቅና ሰጠ

You are currently viewing የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ ለስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎች መስፋፋት ላደረጉት አስተዋጽኦ እውቅና ሰጠ

AMN – ሐምሌ1/2016ዓ.ም

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ ለስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎች መስፋፋት እና ለሴት እና ወንድ ብሔራዊ ቡድኖች ላደረጉት ድጋፍ እውቅና ሰጥቷል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የበላይ ጠባቂ እንዲሆኑም የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሾሟቸዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በእውቅና መርሐ-ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፣ ከ2010 ዓም በፊት በአዲስ አበባ ከተማ የነበሩት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች 495 ብቻ የነበሩ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 160ዎቹ ብቻ የእግር ኳስ ሜዳ ነበሩ።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በከንቲባ አዳነች አቤቤ የሚመራው የከተማው አስተዳደር ለመስኩ በሰጠው ትኩረት 1199 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በከተማዋ የተገነቡ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 351 የእግር ኳስ ሜዳ መሆናቸውን ፌዴሬሽኑ አረጋግጧል ብለዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍ እንዲሁም ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የሴካፋ ሻምፒዮን ሲሆን ከንቲባ አዳነች ድጋፍ እና ማበረታቻ መስጠታቸውን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ቡድኑ ደረጃውን የጠበቀ ሜዳ በማጣት በውጭ ሀገራት ውድድር ለማድረግ የተገደደበትን ሁኔታ ለመለወጥ የአቃቂ ስታዲየም የፊፋ እና የካፍ ደረጃዎችን አሟልቶ አለም አቀፍ እስታዲየም ግንባታው በፍጥነት እንዲካሄድ አመራር መስጠታቸውንም ተናግረዋል።

ከንቲባ አዳነች በነዚህ እና በሌሎች መስኮች ለእግር ኳሱ እድገት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የፌደሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እውቅናው እንዲሰጣቸው መወሰኑንም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

ለተሰጣቸው እውቅና ምስጋና ያቀረቡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስተዳደራቸው አዲስ አበባን ህጻናትን ለማሳደግ ምርጥ አፍሪካዊት ከተማ የማድረግ ራዕይን ማስቀመጡን ተናግረው በሁሉም መስክ የነገ ጠንካራ ሀገር ተረካቢዎችን ለማፍራት በህጻናት ላይ ኢንቨስት እያደረግን ነው ብለዋል።

የተሰጣቸው እውቅና እና የብሔራዊ ቡድን የበላይ ጠባቂነትም የበለጠ ለመስራት የሚያነሳሳ የህዝብ አደራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በሰብስቤ ባዩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review