የኢትዮጵያ ኮምፕርሄንሲቭ ዩኒቨርሲቲዎች ማህበር በይፋ ተመሰረተ

You are currently viewing የኢትዮጵያ ኮምፕርሄንሲቭ ዩኒቨርሲቲዎች ማህበር በይፋ ተመሰረተ

AMN – መጋቢት 2/2017 ዓ.ም

በኮምፕርሄንሲቭ አደረጃጀት የተመደቡ ዩኒቨርሲቲዎች ማህበር መሰረቱ።

የማህበሩ የምሥረታ ጉባኤ በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት በባሌ ሮቤ ተካሂዷል።

ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲዎች በሚያካሄዱት ተግባር ውጤታማ እንዲሆኑ በምርምር “አብላይድ እና ኮምፕሬሄንሲቭ” ብሎ ማደረጀቱ ይታወሳል።

ማህበሩን የመሰረቱት በኮምፕሬሄንሲቭ አደረጃጀት ስር የተካተቱ 21 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው።

የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አነጋግረኝ ጋሻው (ዶ/ር) የማህበሩ ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ዩኒቨርሲቲዎች ተቀናጅተው መስራታቸው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

በዚህም ዩኒቨርሲቲዎቹ በአደረጃጀቱ የተሰጣቸውን ተልዕኮ የሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።

ለማህበሩ ውጤታማነት ሚኒስቴሩ እገዛ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

የማህበሩ ሰብሳቢ አነጋግረኝ ጋሻው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ አዲሱ አደረጃጀት ዩኒቨርሲቲዎች በተሰጣቸው ተልዕኮ ውጤታማና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያግዛል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ ማህበር መመስረታቸው ከተናጥል ይልቅ ተግባራትን በማቀናጀት ተወዳዳሪና ውጤታማ ሥራ ለመስራት ያስችላል ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች መካከል ልምድ፣ መለዋወጥ እና በትብብር ለመስራት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው በመረዳት ሁሉም የማህበሩ አባል ዩኒቨርሲቲዎች ለስኬቱ እንዲተጉም መለዕክት አስተላልፈዋል።

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አህመድ ከሊል (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ማህበሩ የተቋቋመለትን ተልዕኮ እንዲያሳካ ከሁሉም አመራርና ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የማህበሩ ምሥረታ ምርምርና ሌሎች ተግባራት ላይ ልምድ ለመለዋወጥና ውጤታማ ስራ ለመስራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በመስራች ጉባኤ ተሳታፊ የማህበሩ አባል ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review