የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ላይ ማሻሻያ ተደረገ
AMN- ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም
በትናንትናው ዕለት ይፋ በተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ላይ የዋጋ ማሻሻያ አደረገ።
በማሻሻያው መሰረት የውጭ ምንዛሬው በገበያ እንደሚወሰን እና ብሔራዊ ባንክ የቁጥጥር ሥራውን ብቻ እንደሚሠራ ተገልጿል።
ከማይክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ መካከል የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ አንዱ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚሁ መሰረት ከዛሬ ጀምሮ የዋጋ ማሻሻያው ተደርጓል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ፥ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ማሻሻያው የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ያሻሽላል።
የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ ገቢ በሚያስገኙ ዘርፎች የተሠማሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ይጠቅማል ተብሏል።
በመግለጫው እንደተጠቀሰው ማሻሻያው የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ገቢ በተገቢው መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን እንዲሁም ለነዋሪዎችና ለአምራች ዘርፉ ጥቅም መዋሉን ለማረጋገጥ ያስችላል።
በተጨማሪም፥ የገቢ ምርቶች አስመጪዎች እና የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች የገበያ ድርሻቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳል።
ማሻሻያው የግሉን ዘርፍ ለማሳደግ እና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማዘመን እንዲሁም ኢኮኖሚውን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ የተወሰዱ ሌሎች በርካታ የማሻሻያ እርምጃዎችን የሚደግፍና የሚያጠናክር እንደሚሆንም ተገልጿል።
ማሻሻያው የውጭ ኢንቨስተሮችን በመሳብ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ፣ የንግድ ሥርዓታችንንም ከአጎራባችና ከአቻ ሀገራት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ በመግለጫው ተጠቅሷል።