AMN- ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም
የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚያደርገው የአምስት ዓመት መርሃ ግብር ወደ ስራ ሊገባ መሆኑ ተገለጸ።
ለመርሃ ግብሩ ተፈጻሚነት አጋር አካላት 808 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ከእ.አ.አ 1952 አንስቶ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
‘ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ የሚተገብረው የአምስት ዓመት መርሃ ግብር ሰነድ ይፋ ማድረጊያ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
በውይይቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ዋና ተወካይ አቡበከር ካምፖ፣በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ምክትል ተወካይ ማሪኮ ካጎሺማ፣ የፌደራል መንግስት እና የክልል አመራሮች እንዲሁም የልማት አጋሮች ተገኝተዋል።
የዩኒሴፍ የኢትዮያ የአምስት ዓመት መርሃ ግብር ሰነድ አስመልክቶ ገለጻ ተደርጓል።
ከእ.አ.አ 2025 እስከ 2030 ፕሮግራሙ እንደሚተገበር ተመላክቷል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የሚደግፍ መሆኑን ገልጸዋል።
ተጋላጭ የሆኑት ማህበረሰቦች ፕሮግራሙ የጤና፣ ትምህርት፣ የሕጻናት ጥበቃ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ስትራቴጂካዊ የውሃ እና ንጽህና ፕሮግራም (WASH Climate Resilient Development) እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።
መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያ እና ዩኒሴፍ በዋና የትኩረት መስኮች ላይ ያላቸውን ትብብር እንደሚያጠናክር አመልክተዋል።
የዩኒሴፍ የኢትዮያ የአምስት ዓመት መርሃ ግብር ሰነድ የድርጅቱ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ እ.አ.አ በየካቲት ወር በኒው ዮርክ በሚያደርገው ስብሰባ ሰነዱን ያጸድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል።
መርሃ ግብሩ በፌደራል እና በሁሉም ክልሎች ደረጃ እንደሚተገበር ተጠቁሟል።
አጋር አካላት ለመርሃ ግብሩ ትግበራ 808 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።