የዲጂታል አሰራር መዘርጋቱ ለሌብነት እና ለብልሹ አሰራሮች በር ዘግቷል-የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ

AMN – ጥር 2/2017 ዓ/ ም

የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን እና ዲጂታል አሰራር በመዘርጋት የተገልጋዩን እንግልት የሚቀንሱ በርካታ ውጤቶች ማስመዝገቡን እና ለሌብነት እና ለብልሹ አሰራሮች በር መዝጋቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ገለፀ።

የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ለኤ.ኤም.ኤን ዲጂታል እንደገለፀው ፣ቢሮው በዋናነት አገልግሎቱን በኦንላይን የሚሰጥ በመሆኑ የተገልጋዩን ጊዜ፣ ገንዘብ እና ጉልበት በመቆጠብ ፍትሃዊ እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል።

የኦንላይን አሰራር ስርዓት መዘርጋቱ የመሬት ልማት አስተዳደሩ ቢሮ ንግድ ባንክን እና ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ ከ33 በላይ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን በማስተሳሰር አሰራሩን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት ለተገልጋዮች የተሳለጠ እና የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት ማስቻሉንም ቢሮው ገልጿል፡፡

የኦንላይን አገልግሎት መጀመር የሪፎርሙ አካል መሆኑንም ጠቁሟል ።

የክፍያ ስርዓት ሙሉ በሙሉ ዲጂታል እና በኦንላይን መደረጉ ተገልጋዩ ቢሮ ድረስ በአካል መገኘት ሳያሥፈልገው፣ አገልግሎቶቹን በቤቱ ሆኖ በእጁ ባለ ስልክ አማካኝነት፣ በተመቸው ጊዜና ሰዓት፣ በትንሽ ወጪ ቀልጣፋ አገልግሎት መሰጠት መጀመሩን ቢሮው አስታውቋል።

ሰነዶች ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የታገዙ መደረጋቸው እና ከወረቀት አገልግሎት መውጣት መቻሉ ዋና ዋናዎቹ አገልግሎቶች መገለጫዎች መሆናቸውን ነው ቢሮው የገለፀው።

በዚህም አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ መተካታቸው እና ይህም ተገልጋዩ የጨረታ ሰነዶችን ለመግዛትም ሆነ ክፍያ ለመፈፀም ሲል የሚደርሥበትን እንግልት መቅረፍ መቻሉን ቢሮው ገልጿል።

ይህም የህግ ማዕቀፍ ወጥቶለት የፀደቀ በመሆኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱ የሰነድ ማጭበርበርን፣ ብልሹ አሰራርን፣ የዶክመንቶች ስወራን፣ እና የተገልጋዮችን እንግልት ከማስቀረት ባሻገር ፍትሃዊና መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንጻር የጎላ ሚና እንዳለው ተመላክቷል።

በዚህም ተበታትነው የነበሩ ወደ 12 የሚጠጉ የህግ ማቀፎችን ወደ ሁለት በማውረድ በተበታተነ እና ባልተደረጀ መልኩ የነበሩትን ወደ አንድ ማእከል ማምጣት መቻሉን ተጠቁሟል።

በቢሮው በኩል አገልግሎቱን ለማሳለጥ እና ማቀላጠፍ ታስቦ ለተሰራው ስራ መሳካት ከከተማ አስተዳደሩ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የደረገለት ድጋፍም ቀላል እንዳልነበረ ቢሮው አስታውሰዋል።

በዚህም በቢሮው እና በማይክሮፋይናንስ ተቋማቱ መካከል የተፈጠረው የአገልግሎት አሰጣጥ ትስስር ተቋማቱ መረጃዎችን በቀጥታ መለዋወጥ እና ማረጋገጥ እንዲችሉ ግልፀኝነትን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል እድል የፈጠረ እንደሆነ ተነግሯል።

በተቋሙ የተሰራው ሪፎርም የተቋሙን የቀድሞ ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ሌሎች ልምድ የሚቀምሩበትም ማዕከል መሆን እንደቻለ ቢሮው አስታወቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል መቀየሩ ይታወሳል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review