በክረምት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ለስጋት ከሚዳርጉ ጉዳዮች መካከል የጎርፍ ተጋላጭነት አንዱ ነው፡፡ በተለይ የወንዝ ዳርቻዎች ለችግሩ የመጋለጥ ዕድላቸው ያይላል። አደጋው በየትኛውም ቅፅበት የሚያጋጥም መሆኑ ደግሞ የባሰ አስጨናቂ ያደርገዋል፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት በላፍቶ ክፍለ ከተማ መካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በተፈጠረ ጎርፍ የበርካታ ቤተሰብ አባላት ከነቤታቸው መወሰዳቸው ይታወሳል። የመካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ ኮሌጅ ቅጥር ግቢም ሙሉ በሙሉ በጎርፍ ተጥለቅልቆ በውስጡ የነበሩ የ7 ሰዎች ሕይወት ማለፉ አይዘነጋም፡፡
መጋቢት 9 ቀን 2015 ዓ.ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ማንጎ ሰፈር ተብሎ በሚጠራ መንደር ያጋጠመው ችግርም ሌላው አስደንጋጭ አደጋ ነበር፡፡ በወንዝ ዳርቻ ላይ የነበሩ ቤቶች በጎርፍ በመጥለቀለቃቸው በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የነበሩ የ3፣ የ13፣ የ15 ዓመት ልጆችና የ46 ዓመት እናት በጎርፉ መወሰዳቸው ይታወሳል፡፡ እነዚህ 4 ሰዎች በጎርፍ መወሰዳቸውን ተከትሎ በወቅቱ በአስክሬን ፍለጋ ላይ የተሰማሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የዋናተኛ ቡድኖች የ3 ዓመት ህጻን አስክሬን ማግኘታቸው አሰቃቂ ክስተት ሆኖም ነበር፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 በተለምዶ ሱማሌ ተራ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ አንዱ የጎርፍ ተጋላጭ ቦታ ነበር፡፡ በዚህ አካባቢ የሚገኘውና ምንዳ የሚባለው ወንዝ የድጋፍ ግንብ ሳይሰራለት በፊት ሞልቶ የፈሰሰባቸው ጊዜያት መኖራቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ። በዚህ ምክንያትም የክረምት ወቅት ሲመጣ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደሚገቡ የነገሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ከጎርፍ ስጋቱ ባለፈ፣ ወንዙ የሞቱ እንሰሳትንና የተለያዩ ቆሻሻዎችን ይዞባቸው ስለሚመጣ በመጥፎ ጠረን ሲሰቃዩ መኖራቸውንም አስታውሰዋል፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎቻችን መካከል አንዷ የሆኑትና በአካባቢው ከ40 ዓመት በላይ መኖራቸውን የነገሩን ወይዘሮ ትርንጎ ወንድምገዛው መኖሪያ ቤታቸው ወደ ወንዙ ዳርቻ የተጠጋ በመሆኑ ክረምት በመጣ ቁጥር ስጋታቸው እንደሚጨምር ተናግረዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ትርንጎ ገለፃ፣ ምንዳ ተብሎ የሚጠራው ወንዝ በክረምት ወቅት እየሞላ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በመግባት በተደጋጋሚ በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ ለተለያዩ ጉዳዮች ከሰፈር ርቀው በሄዱ ቁጥር “ምን ይፈጠር ይሆን? ወንዙ ድንገት ሞልቶ ልጆች ላይ ጉዳት አድርሶ ይሆን? ቤታችን ፈርሶ ይጠብቀኝ ይሆን?” የሚል ስጋት ይሰማቸው እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን የወንዝ ዳርቻ ድጋፍ ግንብ በመገንባቱ መጠነኛ እፎይታ እንደተሰማቸው ገልፀዋል፡፡
ወይዘሮ መዲና ከድር የተባሉት ሌላዋ የአካባቢው ነዋሪም ለዓመታት በቆየው የጎርፍ ስጋት ምክንያት በመጨነቅ እንቅልፍ ሳይተኙ ያድሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ከ20 አመት በፊት ወንዙ ሞልቶ በመፍሰስ የእሳቸውን ጨምሮ በአካባቢው ያሉ 9 መኖሪያ ቤቶችን ጠራርጎ ወስዶባቸው ቀበሌ እስከመጠለል መድረሳቸውን የሚያስታውሱት እኚህ እናት፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ “ያ አደጋ ዳግም ይከሰት ይሆን?” በሚል ስጋት ውስጥ መቆየታቸውንና አሁን ግን ችግሩ መቃለሉን አስረድተዋል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመከላካል ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት የድጋፍ ግንቦችን መገንባትና ነዋሪዎችን የማንሳት ስራ ሲሰራ መቆየቱን የክፍለ ከተማው ውበትና አረንጓዴ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተካ ደመቀ ገልፀዋል፡፡
በዘንድሮው የክረምት ወቅትም በክፍለ ከተማው በወረዳ 1፣ 2፣ 4፣ 6 እና 7 ውስጥ የሚገኙና ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች መለየታቸውን አስታውሰው፣ ከእነዚህም በከፍተኛ ስጋት ውስጥ በነበሩ ሶስት ወረዳዎች ክረምቱ ከመግባቱ በፊት እልባት ለመስጠት በትኩረት መሰራቱን አስረድተዋል፡፡
በእነዚህ ወረዳዎች በቅድሚያ ተነሺ ነዋሪዎች የስነ ልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉ ግንዛቤ ከመፍጠርና ከማስተማር ባለፈ ተጋላጭ ተብለው በተለዩ አካባቢዎች 370 ካሬ ሜትር ርዝመት ያለው የድጋፍ ግንብ መገንባቱን አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ አቶ በኃይሉ ብዙነህ የተባሉ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪ እንደሚሉት፣ በከተማዋ በተለይ በክረምት ወቅት ለሚፈጠረው የጎርፍ አደጋ ማህበረሰቡ በሚፈፅመው ያልተገባ ድርጊት ምክንያት የሚፈጠር ሰው ሰራሽ ችግር ስለመሆኑ የተለያዩ ማሳያዎችን በማንሳት አስረድተዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለፃ፣ ለጎርፍ አደጋ መከሰት አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ ከሚገኙ ምክንያቶች መካከል በፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ውስጥ የሚጣሉ ልዩ ልዩ የፕላስቲክ ቁሶች ይጠቀሳሉ፡፡ እኛም እንደታዘብነው በተለይም እሽግ ውሃ የሚቀርብባቸው የፕላስቲክ ኮዳዎች እና የእቃ መያዣ ፔስታሎች በቀላሉ የማይበሰብሱና ባሉበት ሁኔታ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ በመሆኑ፣ የጎርፍ መውረጃ መስመሮች እንዲደፈኑ እና ጎርፍ ወደ መንገድ ገንፍሎ በመውጣት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲያደርስ ምክንያት ሆኗል፡፡
በተመሳሳይ በእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራራ ኮሚሽን የአቃቂ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር ተስፋዬ ቀነኒሳ በክፍለ ከተማው ወረዳ 1፣ 2፣ 3፣ 4ን ጨምሮ በርካታ የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች መኖራውን ጠቅሰው፣ ከእነኝህም በተለምዶ መስጂድ ሰፈር፣ መጋላ ሰፈር፣ አጂፕ፣ በሰቃ ትምህርት ቤት አካባቢ፣ ህንድ ግቢና ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡
አካባቢዎቹ ያላቸውን የተጋላጭነት ደረጃ በመለየት መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ያስታወሱት ኃላፊው በተለይ በገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ የነበረው ስጋት መንገዱ በመሰራቱ ሙሉ በሙሉ ችግሩ መቃለሉን አስረድተዋል፡፡ እንደዚሁም በተደጋጋሚ ለጎርፍ ተጋላጭ በነበረው በአቃቂ ወንዝ አካባቢ የሚገኘው መስጂድ ሰፈርም የወንዙን አቅጣጫ የማስቀየስ ስራ ከመሰራቱም ሌላ በሌሎች አካባቢዎችም የውሃ መውረጃ ቱቦዎችን በማስጠረግ ጊዜያዊ መፍትሔ ለመስጠት ጥረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው ከተባሉት አንዱ በሆነው አጂፕ ሰፈር ነዋሪዎችን ከአደጋ ስጋት ነፃ ወደ ሆነ አካባቢ ለማስፈር ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ሳይገልፁ አላለፉም፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራረር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ በከተማዋ 135 የሚጠጉ የጎርፍ ተጋላጭ ቦታዎችን በመለየት መፍትሄ ለሚሰጡ ተቋማት ምክረ ሃሳብ መስጠቱን አስታውሰዋል፡፡ የምክረ ሃሳቡ ማጠንጠኛም በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ከቦታቸው እንዲነሱ፣ በወንዝ ዳርቻዎች የድጋፍ ግንብ እንዲሰራ፣ የጎርፍ መውረጃ ቱቦች እንዲፀዱና መስመሮችን መጥረግ እንደሚገባ የሚያሳስብም ነው፡፡
አቶ ንጋቱ በማብራሪያቸው፣ በከተማዋ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት የድጋፍ ግንብ መገንባት፣ የፍሳሽ ቆሻሻ ጠረጋና ነዋሪዎችን የማንሳት ስራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው፣ “በዚህም መልካም ሊባል የሚችል ውጤት ተገኝቷል፡፡ ለአብነትም የዘንድሮው የክረምት ወቅት ከገባ ጀምሮ በግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች ላይ መጠነኛ ጉዳት ከማድረሱ ውጪ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት አልደረሰም” ብለዋል፡፡
በሰው ህይወት ላይ ጉዳት አለመድረሱ በጎ ነገር ቢሆንም የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ትንበያን ዋቢ በማድረግ በዘንድሮው የክረምት ወራት የተጠናከረ ዝናብ እንደሚኖር ጠቅሰው፣ ማህበረሰቡ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ሲሰሩ ከነበሩ ስራዎች ዋና ዋናዎቹ ተጋላጭ ቦታዎችን መለየት አንዱ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ንጋቱ፣ እነዚህን ተጋላጭ ቦታዎች ከኮሚሽን መስሪያ ቤቱ ጋር በትብብር ለሚሰሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለስልጣን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ፅህፈት ቤት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ጨምሮ ለጉዳዩ መፍትሄ ለሚሰጡ ተቋማት እንዲደርሳቸው ተደርጎ ተቋማቱ እንደየስራ ባህሪያቸው መፍትሄ እንዲሰጡ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
በሸዋርካብሽ ቦጋለ