ወይዘሮ ሰዓዳ ሀሰን በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አያት ተብሎ የሚጠራ መንደር ነዋሪ ናቸው። የቀድሞ የቅጥር ስራቸውን አቁመው ለበርካታ ዓመታት የቤት እመቤት በመሆን ልጆች ሲያሳድጉ መቆየታቸውን ይናገራሉ። ልጆቻቸው አድገው ትምህርት ቤት መዋል ሲጀምሩ ወደ ቀደመ ስራቸው መመለስ ቢፈልጉም በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካላቸው ይቀራል። በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ እያሉ የሌማት ትሩፋት ተግባር ተጀመረ። እርሳቸውም ሳይውሉ ሳያድሩ በመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ሆኑ። እነሆ አሁን ከመኖሪያ ቤታቸው ርቀው ሳይሄዱ ባላቸው ክፍት ቦታ በሚሰሩት የከተማ ግብርና የቤት ውስጥ ፍጆታ ከማሟላት አልፈው ለቤተሰቡ መተዳደሪያ የሚሆን ተጨማሪ ገቢ በማስገባት ላይ ይገኛሉ።
በዶሮ እርባታ የከተማ ግብርና ስራን እንደጀመሩ የሚናገሩት ወይዘሮ ሰዓዳ፣ በየሳምንቱ እስከ 40 እንቁላል ያገኛሉ፡፡ ለቤት ውስጥ ፍጆታ ከሚጠቀሙት ባሻገር ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ኑሮአቸውን መደጎም ችለዋል፡፡ ከዶሮ እርባታው ጎን ለጎንም እንደ ቆስጣ፣ ሽንኩርት፣ ካሮት፣ ቃሪያና ጎመን የመሳሰሉ የከተማ አትክልቶችን ባላቸው ክፍት ቦታ በማምረት ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ላይ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ ሰሚት ኮካ ኮላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ለገሰ ገላኖ ምንም እንኳን የከተማ ነዋሪ ቢሆኑም የኑሮአቸው ዋነኛ መሰረት ግብርና እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡ እኝህ አባት በመኖሪያ አካባቢያቸው ጤፍና ስንዴ አምርተው ከመጠቀም ጀምሮ ከብት በማደለብ፣ የወተት ላም እርባታ፣ ዶሮ እርባታና የጓሮ አትክልቶች ልማት ላይም ተሰማርተው የተሻለ ኑሮ በመኖር ለአካባቢው ማህበረሰብ አርአያ ሆነዋል፡፡
መንግስት ምርጥ ዘርና ማዳበሪያን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግላቸው የገለፁት አቶ ለገሰ፣ በዚህም የተሻለ ውጤት እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በያዝነው ዓመት ብቻ 70 ኩንታል ስንዴ፣ 80 ኩንታል ጤፍ፣ በርካታ ኩንታል አትክልትና ፍራፍሬ ማግኘታቸውን አክለው ገልፀዋል፡፡
አሁንም ለገበያ የደረሱ ካሮት፣ ቀይስር፣ ጎመን፣ ቃሪያና ቆስጣ የመሳሰሉ የጓሮ አትክልቶች እንዳሏቸው ጠቅሰው፣ እነኝህንም በሰንበት ገበያዎች አመካይኝት ለሸማቹ ማህበረሰብ በተመጣጣን ዋጋ ተደራሽ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ በከተማ ግብርና ስራ የተሰማሩት አቶ ዋለ አየለም ዘርፉ የቤተሰብን የምግብ ፍጆታ ከመሸፈን ባለፈ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ገበያን በማረጋጋት ረገድ አይነተኛ ሚና እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በከተማ ግብርና ስራ ተሰማርተው የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በዘርፉ ከተሰማሩበት ወቅት አንስቶ፣ ለቤተሰባቸው ፍጆታ የሚያስፈልጉ የጓሮ አትክልቶችን ከደጃፋቸው እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡
አቶ ዋለ አየለ
በተለይ ከሁለት አመት ወዲህ ከጓሮ አትክልቶች በተጨማሪ ዶሮ በማርባትና ንብ በማነብ ይበልጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ ዋለ፣ ጫጩቶችን በማሳደግ ለዶሮ አርቢዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በማከፋፈል የተሻለ ገቢ እያገኙ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በወር ውስጥ በትንሹ ሁለት ጊዜ በእሁድ ገበያዎች የጓሮ አትክልቶችን በማቅረብ በሺህ ብሮች የሚቆጠር ገቢ እንደሚያገኙ ጠቁመው፣ ንብ በማነብም በዓመቱ ወደ 70 ኪሎ ግራም የማር ምርት እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡
ወጣት ተረፈ ኃይሉ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ውስጥ በሚገኝ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በጥበቃ ስራ ይተዳደራል፡፡ ከጥበቃ ስራው ጎን ለጎንም መደበኛ ስራውን በሚያከናውንበት አካባቢ ባለው ክፍት ቦታ በከተማ ግብርና ስራ ተሰማርቶ ተጨማሪ ገቢ እያገኘ ኑሮውን እንደሚደጉም ነው የነገረን፡፡ “የስራ ትንሽ የለውም የሚለው ወጣት ተረፈ በዘርፉ ተሰማርቶ ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የእንሰት ተክል (ኮባ) ቃሪያ፣ ጎመንና ሰላጣ የመሳሰሉ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ለአካባቢው ነዋሪዎች በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ ማግኘቱን ተናግሯል፡፡
የከተማ ግብርና በአግባቡ ከተተገበረ የቤተሰብን የምግብ ፍጆታ ከመሸፈን ባለፈ ገበያውን እንደሚያረጋጋ የዘርፉ ተሳታፊዎች ይናገራሉ፡፡ ሁሉም ሰው ባለው ውስን ቦታ አምርቶ መጠቀም እንደሚችልም ከራሳቸው ልምድ በመነሳት ሀሳባቸውን አጋርተውናል። ሸማቾችም ይህንኑ ይናገራሉ፡፡ ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኝ የቅዳሜና እሑድ ገበያ አስቤዛ ሲሸምቱ ያገኘናቸው ወይዘሮ ማርታ ጉደታ በገባያው ውስጥ ትኩስና ዋጋውም ተመጣጣኝ የሆነ ምርት እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
ወይዘሮ ማርታ ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ የነበረውን የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ ውድነት አስታውሰው፣ በከተማ ግብርና የተገኙ ምርቶች በሸማቹ ላይ የነበረውን ጫና ከማቃለል አንፃር አስተዋፅኦ እንደነበረው ይሰማኛል ብለዋል፡፡
እንደ ከተማ በእህል ምርትና ጥራጥሬ ዋጋ ላይ በቂ መሻሻል ባይታይም በአትክልት ላይ የመጣው የዋጋ መሻሻል የከተማ ግብርና በስፋት እየተከናወነ በመሆኑ ነው የሚሉት ወይዘሮ ማርታ፣ ለወደፊቱም ስራው በአይነትና ስብጥር ተጠናክሮ ቢቀጥል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የእፅዋት ልማት ኃላፊ አቶ ጋቲሶ ቦጃሞ በበኩላቸው፣ በከተማዋ የከተማ ግብርናን ለማስፋፋት ከሌማት ትሩፋት ጋር በማስተሳሰር በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡
እንደ ከተማም የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማጎልበት በየብሎኩ ነዋሪዎችን ያማከለ እቅድ ተግባራዊ በማድረግ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቁመው፣ በዚህም የዘርፉ ተሳታፊዎችን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ገበያውን በማረጋጋት ረገድም እመርታዊ ውጤት እየታየ መሆኑን ገልፀዋል። አክለውም፣ የከተማ ግብርና የሚጠበቅበትን ያህል ውጤታማ እንዲሆንም በዘርፉ ለተሳተፉ አርሶ አደሮች ምርጥ ዘር፤ የውሃ ፓምፕ፣ የሙያና የቴክኒክ ድጋፍ በመደረጉ ውጤታማ የእንስሳትና የጓሮ አትክልት ልማት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ አቶ ጋቲሶ ገለፃ፣ የከተማ ግብርና በምግብ ራስን ለመቻል፣ ገበያውን ለማረጋጋት አይነተኛ ድርሻ አለው፡፡ እንደ ከተማም የከተማ ግብርናን ባህል ለማድረግና ልምዱን ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ በመሆኑ በእንቁላል ምርትና በጓሮ አትክልት ረገድ በተጨባጭ ለውጥ መጥቷል፡፡ 16 ብር ደርሶ የነበረው የአንድ እንቁላል ዋጋ አሁን ዝቅ ብሏል፡፡ የቀይ ሽንኩርት ዋጋም ቀንሷል። በተመሳሳይ ቆስጣ፣ ሰላጣ፣ ቃሪያና ጎመን የመሳሰሉ የጓሮ አትክልቶች ላይም በጥራት፣ በዋጋ እና በአቅርቦት ረገድ የሚበረታታ ውጤት ታይቷል፡፡
የከተማ ግብርና የህዝብን ህይወት በመቀየር የኑሮ ውድነቱን በመቀነስ ረገድ አይነተኛ ሚና እንዳለው ያመላከቱት አቶ ጋቲሶ፣ በዚህም ማህበረሰቡ ላይ የኑሮ ውድነት የሚፈጥረውን ጫና በማስቀረትና የስራ ባህልን በማሳደግ ብሎም የአመጋገብ ባህልን በመቀየር ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግም በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች ባለው ክፍት ቦታ እና በአገለገሉ የፕላስቲክ ቁሶች እንዲሁም በሽቅብ እርሻ ጭምር የጓሮ አትክልቶችን የማልማቱ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በዘርፉ እንደ አዲስ ከሚቀላቀሉት በተጨማሪ ነባሮችን ለማስቀጠል አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ 511 ሺህ ነባር የከተማ ግብርና አልሚዎች መኖራቸው ተጠቁሟል። እነዚህ ወገኖች በኑሮአቸው ላይ ለውጥ ከማምጣት ባለፈ ገበያውን በማረጋጋት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ እንደሆነም ተነግሯል፡፡
በዚህ ዓመት በማሳ 30 ሺህ 933 ነጥብ 98 ቶን እና ከጓሮ ግብርና ደግሞ 12 ሺህ 202 ነጥብ 24 ቶን አትክልትና ፍራፍሬ ተሰብስቧል። በተጨማሪም በበጀት አመቱ ወደ 29 ሄክተር መሬት በበጋ ስንዴ ተሸፍኖ 201 ነጥብ 8 ቶን ምርት ተገኝቷል፡፡ የምርት መጠኑ ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጠቱ ተገልጿል፡፡
በመኸር ሰብልም በስንዴ፣ በጤፍና በተለያዩ የሰብል አይነቶች 16 ሺህ 906 ነጥብ 88 ቶን ምርት የተገኘ ሲሆን፣ በጥቅሉ 60 ሺህ 247 ነጥብ 52 ቶን ምርት በከተማ ግብርና ማግኘት መቻሉን አቶ ጋቲሶ ነግረውናል፡፡
በሸዋርካብሽ ቦጋለ