የፀጥታ አካላት ከህዝብና ከመንግስት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመገንዘብ ተግባራቸውን በብቃት እንዲወጡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው አስገነዘቡ

You are currently viewing የፀጥታ አካላት ከህዝብና ከመንግስት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመገንዘብ ተግባራቸውን በብቃት እንዲወጡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው አስገነዘቡ

AMN- ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም

በ2017 ዓ/ም የተከናወኑ የመስቀልና ኢሬቻ የአደባባይ በዓላት በስኬትና በደማቅ ሁኔታ በመጠናቀቃቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ የተቋሙን አመራርና አባላት አመስገነ ፡፡

በመርሀ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በአዲስ አበባ ፖሊስ የኮሚሽነር ፅ/ቤትና ስታፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር አህመዲን ጀማል በሩብ ዓመቱ ከተከናወኑ አበይት ተግባራት መካከል የ2017 ዓ/ም የአደባባይ ኩነቶች በሠላም በመጠናቀቃቸው የተዘጋጀ የምስጋና ፕሮግራም መሆኑን ገልፀዋል ፡፡

የተገኘው ውጤት ከበዓላቱ በሠላም መጠናቀቅ ባሻገር ለመደበኛው የፖሊስ አገልግሎት ሥራ ትልቅ ግብዓት የተገኘበት ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በዕለቱ ለተገኙ አመራርና አባላት ባደረጉት ንግግር የከተማችንን ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ያለምንም መሰላቸትና ድካም የ2017 ዓ/ም የአደባባይ በዓላት ድምቀታቸውን ጠብቀው በሠላም በመከናወናቸው የተሰማቸውን ልባዊ ኩራት ገልፀው የተቋሙን በየደረጃው ያሉ አመራሮችንና አባላትን አመስግነዋል፡፡

ኮሚሽነር ጌቱ በንግግራቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላትና ከሰላም ወዳዱ የከተማው ነዋሪ ጋር በመቀናጀት በመደበኛነት በሚያከናውነው ሰላምና ፀጥታን የማስጠበቅ ስራ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል፡፡

በዘንድሮ የመጀመሪያ ሩብ አመት በተከናወኑ ህግን የማስከበር ስራዎች የከተማውን ፀጥታ የማወክ የማይሳካ ህልም ያላቸውን ኃይሎች ፍላጎት በመቀልበስ የከተማችንን ሠላምና ደህንነት በማስጠበቅ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በርካታ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀው ለስኬታማ ስራው መላው የፀጥታ አካላቱን አመስግነዋል፡፡

በቀጣይም የፀጥታ አካላት ከህዝብና ከመንግስት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመገንዘብ ተግባራቸውን በብቃት እንዲወጡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው አሳስበዋል፡፡

የምስጋና መርሀ ግብሩ የተከናወነው በአራዳ ክ/ከተማ አስተዳደር የመሠብሰቢያ አዳራሽ ሲሆን የተቋሙ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ አመራርና አባላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review