AMN – የካቲት 5/2017 ዓ.ም
የፋይናንስ ተቋማት ፍትሃዊ አለመሆን አፍሪካን ከህዝቦቿ ጋር፣ የተፈጥሮ ሀብቷን በሚገባ መጠቀም እንዳትችል እንቅፋት ሆኖባታል ሲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ ተናገሩ፡፡
46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ ባደረጉት ንግግርም፣ እኩልነት አለመኖሩ የአፍሪካ ህዝብ ከዓለም የፋይናንስ ሥርዓት እንዲዘገይ፣ ከገበያ ሥርዓት እንዲወጣ እና በተቋማት ግንባታ ወደኋላ እንዲቀር እንዳደረገው አመላክተዋል፡፡
ይህም አፍሪካውያን የተፈጥሮ ሀብታቸውን በአግባቡ መጠቀም እንዳይችሉ ስለማድረጉ ነው የገለጹት።
አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቷ አህጉሪቱን ሳያለማ ወደ ሌሎች አህጉራት መውጣቱ ኢንቨስትመንት እንዳይስፋፋ እና ለኢኮኖሚ ቀውስ እንድትዳረግ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩንም አንስተዋል፡፡
አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የምታሳድረው ተፅዕኖ ጥቂት ቢሆንም የጉዳቱ ገፈት ቀማሽ መሆኗንም ገልጸዋል።
በመሆኑም የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአፍሪካን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ መሻሻል እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት።
የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ስርዓት በመሰረታዊነት መቀየር እንዳለበትም አፅንዖት ሰጥተዋል።
በአህጉሪቱ ጥሬ ሀብትን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ በምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ የመላክ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አፍሪካውያን በንግድ መተሳሰር እንዲችሉም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና መፈጠር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በታምራት ቢሻው