AMN – መጋቢት 4/2017 ዓ.ም
የፌዴራል መንግስት ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ ህጋዊ ጥያቄ አላቀረብኩም ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ርዕሰመስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ፡፡
ርዕሰመስተዳድሩ ይህን ያሉት በዛሬው እለት የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ነው፡፡
የትግራይ ክልል ሲቋቋም የፌዴራል መንግስት በራሱ ተሳትፎ እና ፈቃድ እንደሆነ የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ በህጋዊ መንገድ የተቋቋመ መንግስት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ አደጋውን የመቀልበስ ግዴታ ያለበት የፌዴራል መንግስት ነው ብለዋል፡፡
የክልል መንግስታት አደጋ ሲያጋጥማቸው ሁሉንም አይነት አቅሞች ተጠቅመው መቆጣጠር ሲያቅታቸው የክልሉን ምክር ቤት ጠርተው የፌዴራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ እንደሚጠየቅ የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ አሁን ባለንበት በትግራይ ክልል ግን በምንም አይነት መልኩ ተሰብስቦ ጥያቄ የሚቀርብለት ምክር ቤትም የለም ብለዋል፡፡
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች ላይ የፌዴራል መንግስቱ ሰራዊት የነበረባቸው አካባቢዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደወጣ ያነሱት አቶ ጌታቸው፣ ይህ በመሆኑም የሚፈጠሩ ችግሮች ይኖራሉ ብለዋል፡፡
‘የፌዴራል መንግስት አግባብነት ያላቸውን እርምጃዎች መውሰድ አለበት ስንል ጦር አዝምቶ ጦርነት ይቀስቅስ ማለት አይደለም’ ብለዋል፡፡
አሁን እየታየ ያለው እንቅስቃሴ ወደ ጦርነት የሚያመራ በመሆኑ፣ የፌዴራል መንግስቱ ይህን ለማስቀረት የሚያስችል ሁሉንም አይነት እርምጃዎች መውሰድ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
‘አሁን እያቀረብነው ያለው ጥሪ በትግራይ ውስጥ ሌላ ጦርነት ተከፍቶ ህዝባችን ወደ ሌላ ጦርነት እና መከራ የሚገባበትን ሁኔታ ማስቀረት እንጂ ጦርነት እንግጠም ማለታችን አይደለም’ ብለዋል አቶ ጌታቸው፡፡