ከ100 ዓመት በኋላ ወደ ፓሪስ የተመለሰው ኦሎምፒክ በታሪካዊው የሴይን ወንዝ ላይ በተከናወነ የሰልፍ ትዕይንት አንድ ብሎ ጀምሮ አስተዛዛቢ፣ አስገራሚና አነጋጋሪ ጉዳዮችን እያስመለከተ ቀጥሏል፡፡ ዓለምን በሁለት ጎራ ከፍሎ ነቀፌታና አድናቆት ሲያስተናግድ ከሰነበተው የመክፈቻ ስነ-ስርዓትና የኦሎምፒክ ጨዋታዎችም በመነጋገሪያ ጉዳዮች ታጅበው ቀጥለዋል፡፡
የደቡብ ሱዳን የኦሎምፒክ ቡድን እየተጫወተ የሱዳንን ብሄራዊ መዝሙር ከማሰማት አንስቶ ከተጀመረ የሳምንት ያህል እድሜ ባለው ኦሎምፒክ ላይ ስህተት ተሰርቶባቸው ይቅርታ የተጠየቀባቸው ጉዳዮች በርከት ያሉ ናቸው፡፡ የፓሪስ ኦሎምፒክን የእስካሁን ውሎ በምንቃኝበት በዚህ ጽሁፍም የስፖርት ቤተሰቡን አግራሞት ውስጥ የከተቱ የተወሰኑ ጉዳዮችን እንመለከታለን፡፡
የፓሪስ ኦሎምፒክ መነጋገሪያነት ገና በውድድሩ መክፈቻ ላይ የሚጀምር ሲሆን፣ በዚህም ተሳታፊ ሀገራት በሴን ወንዝ ላይ ሲያልፉ መድረክ መሪዎች ሀገራትን አሳስተው የጠሩበት አጋጣሚ አዘጋጆቹን ትዝብት ውስጥ የጣለ ነበር።በዚህም በእንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ደቡብ ኮሪያን እንደ ሰሜን ኮሪያ መጥራታቸው ቁጣን ቀስቅሷል። ክስተቱ የተፈጠረው የደቡብ ኮሪያ አትሌቶች ሰንደቅ አላማቸውን እያውለበለቡ በሚያልፉበት ወቅት በስህተት ሰሜን ኮሪያ ተብለው ተጠርተዋል።
ደቡብ ኮሪያዊያን በስህተት መጠራታቸው እንዳበሳጫቸው በመንግስታቸው በኩል እና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ተናግረዋል። የፓሪስ ኦሎምፒክ አዘጋጆች እና ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በበኩላቸው፣ ለተፈጠረው ስህተት በኮሪያ ቋንቋ ይቅርታ ጠይቀው ስህተት እንደማይደገም አስታውቀዋል። በስፍራው ያሉት የደቡብ ኮሪያ ስፖርት እና ባህል ምክትል ሚኒስትር ጃንግ ሚራን የተፈጸመው ስህተት እንዳበሳጫቸው ገልጸው፣ ዳግም ስህተት እንዳይፈጠር አስጠንቅቀዋል።
በእርግጥ በፓሪስ ኦሎምፒክ መክፈቻ ላይ የታየው ስህተት የሀገራትን ስም አቀያይሮ በመጥራት ብቻ ያበቃ አልነበረም፡፡ ሌላኛው አነጋጋሪ የሆነው በውድድሩ መክፈቻ ላይ በሊኦናርዶ ዳቪንቺ የተሳለው በክርስትና ዕምነት ዘንድ “የመጨረሻው እራት” በሚል የሚታወቀውን ስዕል በመክፈቻው ላይ መቅረቡ ነው። በርካታ የክርስትና ዕምነት ተከታዮች ስዕሉ የቀረበበት መንገድ ስፖርት ከኃይማኖት ነጻነት አንጻር ስህተት መሆኑን በመናገር መግለጫ እስከማውጣት ደርሰዋል።
ፓሪስን ከቀሪ ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ጋር የሚያገናኙ ፈጣን የባቡር መስመር ላይ የተፈጸመው ጥቃት ታዳሚዎች ላይ እክል ፈጥሯል የሚለውም ሌላኛው የፓሪስ ኦሎምፒክን መነጋገሪያ ካደረጉ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ነው፡፡ በባቡር መሰረተ ልማቱ ላይ ለደረሰው ጥቃት እስከ አሁን ሀላፊነት የወሰደ አካል የሌለ ሲሆን ትራንስፖርቱ አሁንም እንደተቋረጠ እና መንግስትም ይህ ፅሑፍ እስከ ተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ተጠርጣሪዎችን አላሳወቀም።
የኦሎምፒክ አትሌቶች በምግብ እና ትራንስፖርት እጥረት ስለመቸገራቸው ቅሬታ አቀረቡ የሚለው ዜናም ከሰሞኑን የተሰማ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ አትሌቶቹ የምግብ ጥራት እና መጠን ላይ ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን፣ በተለይ የስጋ እና የእንስሳት ተዋጽዖ ምግቦች እጥረት በመኖሩ መቸገራቸውን ነው የገለጹት፡፡ የፓሪስ ኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ በዛሬው እለት ከአትሌቶቹ ጋር ባደረገው ስብሰባ በፈረንሳይ የሚመረቱ የስጋ እና የእንስሳት ተዋጽኦ የምግብ አይነቶች አቅርቦትን እንደሚጨምር ቃል ገብቷል፡፡ ኬር ፎር የተሰኘው ምግብ አቅራቢ ፈረንሳዊ ድርጅት ለ15 ሺህ አትሌቶች በቀን 40 ሺህ ምግብ ለማቅረብ ከአዘጋጆቹ ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል።
የፓሪስ ኦሎምፒክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤቲየን ቶቦይስ መሰል ቅሬታዎች በርካታ ሰዎች በሚታደሙባቸው ሁነቶች ላይ ያጋጥማል፤ አትሌቶች ያቀረቡትን ቅሬታ ለመቅረፍ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ ቅሬታው ከተሰማ በኋላ 700 ኪሎ ግራም እንቁላል እና አንድ ቶን የስጋ ምርት አትሌቶቹ ወደሚገኙበት መንደር እየተጓጓዘ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ሀገራቸውን ወክለው ወደ ፓሪስ የሚሄዱ አትሌቶች በተለየ ፍቃድ ካልሆነ ማረፊያቸው ከሆነው የኦሎምፒክ መንደር ርቀው መሄድ አይችሉም። በፓሪሱ ኦሎምፒክ በውሃ ዋና ለብራዚል ወርቅ ታመጣለች ተብላ የምትጠበቀው ካሮሊና እና በቡድኑ ውስጥ የሚገኘው ፍቅረኛዋ ምሽት ላይ ከኦሎምፒክ መንደሩ መውጣትና ዘና ማለት ፈለጉ። አና ካሮሊና እና ጓደኛዋ ከካምፓቸው በመውጣት ኤፊል ታወር ስር ፎቶ ሲነሱና ለሊቱን ሲዝናኑ ቆይተው እዛው አደሩ።
እናም በማግስቱ እሁድ ይህንን ጉዳይ የደረሰበት የብራዚል ኦሎምፒክ ኮሚቴ አስቸኳይ ውሳኔ በማሳለፍ አትሌቷ ሻንጣዋን እንኳን ከኦሎምፒክ መንደር ሳትወስድ ወደ ሀገሯ በትራንዚት እንድትሄድ ያደረጉበት አጋጣሚም ከኦሎምፒክ መንደር ተሰምቶ ብዙዎችን ያስገረመ ጉዳይ ነው።
ጉዳዩን በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የብራዚል ቡድን ኃላፊ እንዳሉት “እዚህ የመጣነው ልንዝናና አይደለም፡፡ የሁለት መቶ ሚሊዮን ህዝብ አደራ ተሸክመን እንጂ፤ ሆኖም ካሮሊና ከዚህም ቀደም ከቡድን አጋሮቿ ጋር በተደጋጋሚ ትጋጭ የነበረ ሲሆን ከዚህም በላይ ከባዱን ህግ ጥሳ ስለተገኘች ወደ ሀገር ቤት እንድትሸኝ ተደርጓል። የቡድን አጋሯና ፍቅረኛዋም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል። እንዲህ አይነት ምግባረ ብልሹነትን ፈፅሞ አንታገስም” ሲሉ ተናግረዋል።
ሌላኛው ዓለምን እጅ በአፍ ያስጫነው መረጃ ደግሞ አውስትራሊያዊው የሆኪ ተጫዋች በኦሎምፒክ ለመሳተፍ ሲል ጣቱን አስቆረጠ የሚለው ነው፡፡ አንድ የአውስትራሊያ የሆኪ (የገና ጨዋታ ዓይነት ስፖርት) ተጫዋች በፓሪስ ኦሎምፒክ ለመወዳደር ሲል የጣቱን የተወሰነ ክፍል እንዲቆረጥ ማስደረጉ ሲነገር የፓሪሱን የኦሎምፒክ ቆይታ አጃኢብ አስብሎታል።
ማት ዳውሰን ከሁለት ሳምንት በፊት ፐርዝ ውስጥ ቡድኑ ልምምድ በሚያደርግበት ወቅት የቀኝ እጁ ጣት ክፉኛ ከመሰበሩም በላይ ከቀዶ ጥገናው ለማገገም ወራትን ይወስድ ነበር። የ30 ዓመቱ ተጫዋች ግን ለሦስተኛ ጊዜ በኦሎምፒክ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ሲል ጣቱ መገጣጠሚያው ላይ እንዲቆረጥ መወሰኑ የቡድን አጋሮቹን እና አሠልጣኙን አስደንግጧል።
ጉዳት ከደረሰበት ከ16 ቀናት በኋላም አርጀንቲናን ሲገጥሙ አውስተራሊያን ወክሎ ወደ ሜዳ ይመለሳል። ዳውሰን ጉዳቱ በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ጣቱን በመልበሻ ክፍል ውስጥ ሲያየው ራሱን ስቶ እንደነበር ለመገናኛ ብዙኃን ተናግሯል። በፓሪስ ኦሎምፒክ ላይ የመሳተፍ ህልሙ ያከተመም መስሎት ነበር። በአስቸኳይ ከቀዶ ህክምና ሐኪም ጋር ተማከረ። በቀዶ ህክምና ጣቱን ለማስተካከል ቢሞከር ረዘም ያለ የማገገሚያ ጊዜ ከማስፈለጉም በላይ ሙሉ በሙሉ እንደበፊቱ ላይሆን ይችላል ተባለ። ከተቆረጠ ግን በ10 ቀናት ውስጥ ተመልሶ መጫወት እንደሚችል ተነገረው።
ዳውሰን ምንም ዓይነት “ፈጣን ውሳኔ” እንዳይወሰን ባለቤቱ ብታስጠነቅቀውም ባገኘው መረጃ ተደግፎ ውሳኔውን የዚያኑ ዕለት ከሰዓት በኋላ ማሳወቁን ተናግሯል። “በስፖርቱ ያለኝ ጉዞ እየተጠናቀቀ እንጂ እየተጀመረ አይደለም። ማን ያውቃል? ይህ መጨረሻዬ ኦሎምፒክ ሊሆን ይችላል” ሲልም ተደምጧል።
የቡድኑ አምበል የሆነው አራን ዛሌቭስኪ በበኩሉ፣ ውሳኔው በቡድኑ ዘንድ ድንጋጤን ቢፈጥርም ዳውሰንን ደግፈነዋል ሲል ተደምጧል። “በእርግጥ ምን እንደምናስብ አናውቅም ነበር። ሆስፒታል ሄዶ ጣቱን እንደተቆረጠ ሰማን። ይህም በጣም አስገራሚ ነገር ነው” ይላል፡፡ የቡድኑ አሠልጣኝ ኮሊን ባች በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ዳውሰን ከቡድኑ ጋር ልምምድ መጀመሩን ለአውስትራሊያ ሰቭን ኒውስ ሚዲያ ተናግረዋል።
ግብጻዊቷ ስፖርተኛ ናዳ ሀፊዝ የሰባት ወር ነብሰ ጡር ሆና በኦሎምፒክ ተሳተፈች፣ የቻይና ስኬተቦርድ ተጫዋቿ ዜንግ ሃዎሃ በአስራ አንድ ዓመት ከአስራ አንድ ወሯ በኦሎምፒከ ውድድር ላይ ተገኝታለች፤ በዋና ውሃ ጥራት ችግር ሳቢያ የውሃ ዋና ስፖርተኞች ልምምዳቸውን እንዲያቆሙ ተገደዱ፤ የሚሉና ከላይ በጥቂቱ ያነሳናቸውን አነጋጋሪ ጉዳዮችን እያስመለከተ የፓሪስ ኦሎምፒክ ቀጥሏል፡፡ የፓሪስ ኦሎምፒክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤቲየን ቶቦይስ አስተያየት ግን፣ “እጅግ አዝናኙን ኦሎምፒክ ተደሰቱበት” የሚል ሆኗል፡፡ ይህም የበለጠ አስገራሚ አስተያየት ሆኖ ተይዟል፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ