AMN- ጥር 21/2017
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ከ2018 ዓ.ም ጀምሮ የተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ምርጫ ውስጥ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።
ትምህርት ሚኒስቴር ለዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች በዩኒቨርሲቲው ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን የስራ አንቅስቃሴውን አስመልክቶ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርጋዲየር ጀኔራል ከበደ ረጋሣ ዓለም የደረሰበትን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚመጥን በቂ እውቀት ያለው የሰው ኃይል ማፍራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ የዩኒቨርሲቲው ስራ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ እያከናወናቸው ላሉ ሥራዎች በጥናት ላይ የተመሰረተ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ሲሉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ የተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ምርጫ ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲም እንደ አንድ አማራጭ እንደሚካተት ጠቁመዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር እና የፈጠራ ሥራዎች የጀመረውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።