የተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚ ኮሚሽን (United Nations Economic Commission) መረጃ እንደሚጠቁመው፤ የደን ምርቶች ግብይት ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት በማሳየት ላይ ነው፡፡ በጎርጎሮሳውያን የዘመን ቀመር ከ2011 እስከ 2021 በነበሩት ዓመታት ውስጥ የታየው የግብይት መረጃም ዕድገቱን የሚጠቁም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ወደ ገበያው የሚወጣው የእንጨት ምርት መጠን ዕድገት ከማሳየቱ በተጨማሪ፤ በዋጋውም ከፍ እያለ መምጣቱ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
የደን ምርት ግብይት ላይ በከፍተኛ ደረጃ በመሳተፍ ትልቁን ድርሻ ይዘው የሚገኙት ጥቂት አገራት ናቸው፡፡ የኢኮኖሚ ኮምፕሌክስ ኦብዘርቫቶሪ (The Observatory of Economic Complexity) በጎርጎሮሳዊያን የዘመን ቀመር 2022 የነበረውን አፈፃፀም መነሻ አድርጎ ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የደን (እንጨት) ምርትን ወደ ውጭ አገራት በመላክ፡- ካናዳ፣ ሩሲያ፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት የሆኑት ስዊዲንና ፊንላንድም ከቀዳሚዎቹ ተጠቃሾች መካከል ናቸው፡፡
በአንፃሩ፤ ቻይና፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት እና ጃፓን ከሌሎች አገራት ከፍተኛ መጠን ያለውን የእንጨት ምርት ገዝተዋል፡፡ በእንጨት ምርት ግዢ ላይ በቀዳሚነት እየተሳተፉ ያሉትን አገራት የሚያመሳስላቸው አንድ ጉዳይ፤ ወደ አገራቸው የሚያስገቡት የእንጨት ምርት በአብዛኛው ጥሬ ምርት ወይም በከፊል እሴት የተጨመረበት ነው። ይህንን እንደ ግብዓት በመጠቀም በገበያው ላይ ተፈላጊ እና በዋጋቸው ውድ የሆኑ ምርቶችን ያመርቱባቸዋል፡፡
ወደ አህጉራችን አፍሪካ መለስ ብለን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚከናወነው የእንጨት ምርት ግብይት ላይ ያላትን ተሳትፎ ስንመለከት፤ እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ እና ኬንያ የመሳሰሉ አገራትን እናገኛለን፡፡ ከሰሃራ በታች ያሉ አገራትን የንግድ ፍሰት፣ የኤክስፖርት አጋሮች እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ በማውጣት የሚታወቀው World Integrated Trade Solution- WITS ተቋም በ2023 መጨረሻ ላይ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፤ የእንጨት ምርትን በመላክ ደቡብ አፍሪካ ከአህጉሪቱ በቀዳሚነት ተቀምጣለች፡፡
አፍሪካ እንደ አህጉር በደን ሃብቷ የበለፀገች ነች፡፡ ይሁን እንጂ፤ በዓለም አቀፍ ግብይት ላይ ከፍተኛ ገንዘብ የሚንቀሳቀስባቸውን የተለያዩ ምርቶች ለማምረት በግብዓትነት የሚያገለግለውን የደን ሃብት በአግባቡ ማልማት፣ መጠበቅ እና መጠቀም ላይ ሰፊ ክፍተት እንዳለባት የተለያዩ የሰነድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለማሳያነት ተፈጥሮ ለጋስ እጇን ለግሳቸው እጅግ በሚያስደንቅ ገፀ ምድራዊና ከርሰ ምድራዊ ፀጋዎች ከተጎናፀፉት አገራት መካከል የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የሞዛምቢክን ተጨባጭ ሁኔታ ብንመረምር የምንረዳው ሐቅ በእጅጉ የሚያስቆጭ ነው፡፡ እነዚህ አገራት በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ በዋጋም በተፈላጊነትም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ የተፈጥሮ ደን ሃብት ቢኖራቸውም፤ በመሠረተ ልማት እና በሎጂስቲክስ ችግሮች ምክንያት የበይ ተመልካች ከመሆን አልወጡም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፤ ለአህጉሪቱ አገራት ትልቅ የገበያ አማራጭን እንደሚፈጥር ተስፋ የተጣለበትን “የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA)” በአግባቡ መጠቀም ላይ ያለው ችግርም በክፍተትነት ይነሳል፡፡
የኢትዮጵያ የደን ሃብት እና ተጠቃሚነት

ኢትዮጵያ በአግባቡ ካልተጠቀመች ባቸው እምቅ ፀጋዎቿ አንዱ የደን ሃብቷ ነው። የደን ሃብት፤ ከጥሬ ምርቱ ጀምሮ ወደ ብዙ ምርት ተለውጦና እሴት ተጨምሮበት ለገበያ መቅረብ የሚችል ነው፡፡ የደን ሃብት፤ ለሠው ልጅ በመሰረታዊነት ከሚያስፈልጉት ምግብ፣ መጠጥ፣ ልብስ፣ መጠለያ፣ መድሃኒት ጀምሮ ወረቀት፣ የቤትና የቢሮ ቁሳቁስ… እያልን ዘርዝረን የማንጨርሳቸው ምርቶች ዋነኛ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል፡፡
“አንድ የልማት ሥራ ዕድሜ የሚኖረው፣ ዘላቂነቱ የሚረጋገጠው እና አንቱ ሊባል የሚችለው የኢኮኖሚ ፋይዳ ሲኖረው ነው። ልማቱ ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ የገጠር እና የከተማው ነዋሪ በአኗኗሩ ላይ አዎንታዊ ለውጥ የሚያመጣ፣ ምርታማነቱ አድጎ ለኢንዱስትሪ ግብዓት እና ለውጭ ገበያ መቅረብ ከቻለ፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከሌሎች አደጋዎች የሚታደግ… ከሆነ ነው” የሚሉት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር፣ የአየር ጠባይ፣ የአፈር ሁኔታ ስብጥሩ በእጅጉ ተስማሚ ይሁን እንጂ፤ ይህንን ፀጋዋን በአግባቡ ሳትጠቀምበት መቆየቷን በቁጭት ይገልፃሉ፡፡
ኢትዮጵያ ዕምቅ የሆነውን የደን ሃብት ልማት ፀጋዋን ባለመጠቀሟ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ፈሰስ በማድረግ የደን ሃብት ምርት ውጤቶችን ከውጭ አገራት ገዝታ እንደምታስገባ የጠቆሙት አደፍርስ (ዶ/ር)፤ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ እንደ አገር የደን ሃብት ልማት፣ ጥበቃ እና አጠቃቀም ላይ ሰፊና ውስብስብ ችግሮች መኖራቸው እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ይህንን ሃሳብ በጥናታዊ መረጃ አስደግፈው ሲያብራሩም፤ “በጎርጎሮሳዊያን ዘመን ቀመር 2011 የኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት መሪነት ያስጠናው ጥናት መረጃ፤ ኢትዮጵያ በወቅቱ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 152 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ አድርጋለች፡፡ ይህ የደን ምርት ውጤት የሆነውን ወረቀት ሳይጨምር ነው” ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ትኩረቱን በቀርከሃ የደን ዝርያዎች ላይ አድርጎ የሚሠራ እና ቻይናውያን ያቋቋሙት ዓለም አቀፍ ድርጅት በጎርጎሮሳውያን የዘመን ቀመር 2017 ይፋ ያደረገው ጥናት ይህንን እንደሚጠቁም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) አንስተዋል፡፡ እንደሳቸው ማብራሪያ፤ ድርጅቱ የቀርክሃ እና የራታን ኔትወርክ (International Network for Bamboo and Rattan) የሚባል ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ቢሮ አለው፡፡ ይህ ድርጅት ያሠራው ጥናት እንደሚያመለክተው፤ ኢትዮጵያ በአንድ ዓመት ብቻ ግምቱ ከ450 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገንዘብ የፈሰሰበት የደን ምርት ከውጭ አገራት አስገብታለች፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአገራትን የምርቶችን ሽያጭ( Exports) እና የምርቶች ግዥ (Imports) በተመለከተ አሃዛዊ መረጃዎችን በማውጣት የሚታወቀው Trend Economy.com የተሰኘ ገፀ-ድር ከአንድ ዓመት በፊት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፤ የኢትዮጵያ የደን ምርት ሽያጭ እና ግዢ ሁኔታ በአንፃራዊነት መሻሻል እያሳየ መምጣቱን ያሳያል፡፡ እንደመረጃው ከሆነ፤ ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳውያን የዘመን ቀመር 2022 ለዓለም ገበያ ካቀረበችው የእንጨት ምርት ሽያጭ 31 ሺህ ዶላር የሚገመት ገቢ አግኝታለች። ይህ ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ281 በመቶ እድገት አሳይቷል። በአንፃሩ የ3 ነጥብ 15 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የእንጨት ምርቶችን በ2022 ከሌሎች አገራት ገዝታ አስገብታለች፡፡ በደን ምርት ንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ የኢትዮጵያ ዋነኛ አጋሮች ቻይና፣ እስራኤል፣ ጣሊያን እና ኢንዶኔዥያ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ገበያ ከምትልካቸው የእንጨት ምርቶች ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለውን በመግዛት እስራኤል እና ቻይና ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ፡፡
የደን ሃብትን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚያስችል የአገራት ተሞክሮ ያሳያል። በእንጨት ምርት ግብይት ላይ በንቃት የሚሳተፉት የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት ለዘርፉ የሰጡት ትልቅ ትኩረት ካስገኘላቸው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ መካከል የሥራ ዕድል ፈጠራ ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የህብረቱ የኢኮኖሚ ኮሚሽን መረጃ ላይ እንደተጠቆመው፤ በጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር 2020 በእንጨት ላይ ተመስርተው የተቋቋሙ ኢንዱስትሪዎች የሚያንቀሳቅሱት መዋዕለ ነዋይ መጠን ከ136 ቢሊዮን ዩሮ በላይ መድረስ ችሏል። እነዚህ ኢንዱስትሪዎች 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ ይህም ኢንዱስትሪዎቹ በአምራች (ማኑፋክቸሪንግ) ዘርፍ ውስጥ ከተፈጠረው የሥራ ዕድል የ10 ነጥብ 5 ከመቶ ድርሻ እንዲይዝ አስችሎታል፡፡
የደን ሃብት ልማት ከሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች መካከል አንዱ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ መሆኑን የሚጠቁሙት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪው፤ “የደን ልማት ዘርፍ ረዥም እና ብዙ ሂደቶችን የሚያልፍ ነው፡፡ ከችግኝ ማፍላት ጀምሮ ዛፍ ሆኖ ለምርት እስኪደርስ፣ ከዚያም በተለያዩ ፋብሪካዎች በግብዓትነት ጥቅም ላይ ሲውል፣ዓይነተ ብዙ ምርት ሆኖ ለገበያ ሲቀርብ… ባሉት ዋና ዋና ሂደቶች ውስጥ በርካታ ባለድርሻዎች የሚሳተፉበት፣ ብዙ ቁጥር ላላቸው ሠዎች የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት ነው” በማለት አብራርተዋል፡፡
እንደ አገር በደን ልማቱ ዘርፍ፤ ተስፋ ሰጪ ውጤት እንዲመጣ እያደረገ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከወዲሁ እየሰጠ ያለውን የኢኮኖሚ ትሩፋት ለመረዳት የተፈጠረውን የሥራ ዕድል መረጃ መመልከት ይገባል፡፡ ይህንን አስመልክቶ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር)፤ ”ኢትዮጵያ ሰፊ የደን ሃብት ያላት አገር መሆኗን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያለማቋረጥ የተተገበረው እና እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተጨባጭ አሳይቶናል፡፡ የደን ልማት ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችል አይተናል፡፡ ለአብነት መርሃ ግብሩ ባለፉት ዓመታት በችግኝ ማፍላት ሥራ ላይ ለተሠማሩ ከ800 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን መጥቀስ ይቻላል። ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት እንደሚሆንም በይርጋለም በተገነባው ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያሉት የዘይት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በግብዓትነት የሚጠቀሙትን አቮካዶ በብዛት እና በጥራት ማግኘታቸው ምስክር ነው፡፡ የአቮካዶውን በማንጎ፣ በአፕል እና በመሳሰሉት የዕፅዋት ሃብቶቻችን ላይ መድገም አለብን” ብለዋል፡፡
“የአገራችንን ፀጋ በአግባቡ ያላወቅንና ያልተረዳን ሕዝቦች ነን፡፡ ከተትረፈረፉ ፀጋዎቻችን አንዱ የሆነውን የደን ሃብት ጠብቀን፣ ተንከባክበን እና አልምተን ወደ ጥቅም መቀየር ከቻልን፤ ደኖቻችን ብቻ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ትርጉም ባለው ሁኔታ መሸከም ይችላሉ፡፡ የደን ልማት ዘርፉ፤ ልክ እንደ ግብርናው፣ እንደ ቱሪዝሙ፣ እንደ ኢንዱስትሪው … ዘርፍ ሊጠቀስ የሚችል ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የማምጣት አቅም አለው” የሚሉት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪው አደፍርስ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የደን ልማቷን ውጤታማ ካደረገች ሰፊ የገበያ አማራጮችን መጠቀም ትችላለች። ለዚህም እንደ ጂቡቲ፣ ሱማሊያ፣ ሱዳን ያሉ ጎረቤት አገራትን ጨምሮ የደን ምርትን በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀሙ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ሁነኛ የምርቱ መዳረሻዎች ሆነው ያገለግሏታል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ዱባይ ግዙፍ የደን ሃብት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ገንብተው ለአገልግሎት አብቅተዋል፡፡ ለፋብሪካዎቻቸው ግብዓት የሚሆን የደን ሃብት የሚያመጡት ደግሞ ስዊዲንን ከመሳሰሉ የስካንዲቪያን አገራት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በርትታ ከሠራች የስካዲቪያንን የገበያ ድርሻ መሸፈን ትችላለች” ሲሉም አክለዋል፡፡
የደን ሃብት ልማት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ካርቦን እስከመሸጥ የሚያደርስ ስለመሆኑ ”የደን ልማት እንኳን ምርቱ የካርቦን ሽያጩ ብቻ በቢሊዮን ዶላር ገቢ የሚያስገኝ ነው፡፡ አንድ የዛፍ ግንድ ከአጠቃላይ ይዘቱ ግማሽ ያክሉ ካርበን ነው፡፡ ይህ እየተሰላ የሚሸጥበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ ለዚህ የሚሆን የግብይት ሥርዓትም ዓለም አበጅታለች” በማለት የገለፁት አደፍርስ (ዶ/ር)፤ ይህንን ዕድል በአግባቡ መጠቀም ደግሞ ከእኛ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል፡፡
አክለውም፤ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ያስመዘገበችውን ውጤታማነት በደን ሃብት ልማት ላይ ከሠራች ተጠቃሚነቷ ከፍተኛ እና ዘላቂነት ያለው ይሆናል፡፡ ስለዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ “ስንት ተተከለ፤ ስንት ፀደቀ?” ከሚለው አለፍ ብሎ፤ “ከተተከለው ውስጥ ምን ያክሉ ወደ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ገባ” የሚለውን መገምገም እንደሚገባም መክረዋል፡፡
በደረጀ ታደሰ