AMN ህዳር 20/2017 ዓ.ም
ፈረንሳይና አፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ያላቸውን የአጋርነት አድማስ ለማስፋት በጋራ እንደሚሰሩ ገለጹ።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽንና ፈረንሳይ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ምክክር በኅብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ዛሬ ተካሄዷል።
በውይይቱ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማትና የአውሮፓና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን-ኖኤል ባሮትና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
የአፍሪካ ኅብረትና ፈረንሳይ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የሁለትዮሽ አጋርነትና የትብብር ማዕቀፎች አስመልክቶ ውይይት ተደርጓል።
በውይይታቸው የሁለቱን ወገኖች ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ስትራቴጂካዊ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ሰላምና ደኅንነት፣ሽብርተኝነትን መዋጋት፣ ንግድና ኢኮኖሚ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ኢነርጂ ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ሁለቱ ወገኖች ያላቸውን አጋርነት ይበልጥ ለማጎልበት ፍላጎት እንዳላቸው አመልክተዋል።
ፈረንሳይ የአፍሪካ ኅብረትን ተቋማዊ ሪፎርምን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረቱ አጀንዳዎች እንዲሳኩ ድጋፍ እንደምታደርግ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።
ምክክሩ የሁለቱን ወገኖች አጋርነት ይበልጥ ማጠናከርን ያለመ መሆኑም ተገልጿል።
የአውሮፓና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን-ኖኤል ባሮት ከውይይቱ ጎን ለጎን ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት ጋር የጋራ አጋርነትን ማጠናከር ዓላማ ያደረገ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሰላም፣ ደኅንነት፣ ኢኮኖሚ፣ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና ትምህርት ከአፍሪካ ኅብረትና ፈረንሳይ የትብብር መስኮች መካከል በዋናነት ይጠቀሳሉ።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽንና ፈረንሳይ በመደበኛነት ስትራቴጂካዊ ምክክር ማካሄድ የጀመሩት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር በ2019 በፓሪስ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
የአውሮፓና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን-ኖኤል ባሮት ዛሬ ማለዳ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር መወያየታቸው ይታወቃል።