
AMN – ግንቦት 1/2017 ዓ.ም
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከሩሲያ 80ኛ ዓመት የድል በዓል አከባበር በተጓዳኝ ከአገሪቷ ፕሬዝዳንቱ የዓለም አቀፍ ትብብርና ትራንስፖርት ዘርፍ ልዩ አማካሪና ተወካይ ኢጎር ሌቪቲን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ኢትዮጵያና ሩሲያ በሎጂስቲክስና በትራንስፖርት ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እየሰራች የምትገኝበትን ቀጣናዊ የመሰረተ ልማት ትስስር ለማጠናከር ትብብር እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንት ታዬ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ የረጅም ዘመን ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው አውስተው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግንኙነታቸው በይበልጥ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ትልቅ ኢኮኖሚ ያላት አገር መሆኗን በማንሳት፣ የሎጂስቲክስና የትራንስፖርት መሠረተ ልማትን በትኩረት እያስፋፋች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
ሩሲያ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ እና አቅም እንዳላት ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
በዚህ ረገድ የትብብር ቁርጠኝነትን ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል።’

የፕሬዝዳንቱ የዓለም አቀፍ ትብብርና ትራንስፖርት ዘርፍ ልዩ አማካሪና ተወካይ ኢጎር ሌቪቲን በበኩላቸው፤ ተጠናክሮ የቀጠለውን የሩሲያና የኢትዮጵያ ግንኙነት አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ ለሩሲያ በአፍሪካ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላት አገር እንደሆነች ጠቁመው፤ አገራቸው ዲፕሎማሲያዊ ትብብሯን አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የሩሲያ መንግስት በኢትዮጵያ አዳዲስ የሎጂስቲክስና የትራንስፖርት ፕሮጀክቶችን ለመጀመር እና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።