AMN-የካቲት 28/2017 ዓ.ም
ገበያ ከማረጋጋት አኳያ የህግ ማስከበር እና ቁጥጥር ንዑስ ኮሚቴ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን ገለጸ፡፡
ገበያ ከማረጋጋት አኳያ የህግ ማስከበር እና ቁጥጥር ንዑስ ኮሚቴ ግምገማ አድርጓል።
የህግ ማስከበር እና ቁጥጥር ንዑስ ኮሚቴ ሪፖርት ያቀረቡት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ ተስፋዬ ደንድር፣ በኮሚቴው አማካይነት የተለያዩ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን ገልፀዋል፡፡
እርምጃው የተወሰደው ህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውር፣ ህገ-ወጥ የዘይት ዝውውር፣ በህገ ወጥ መንገድ የምርት ክምችት ማካሄድ፣ በአዋኪ ተግባራት እና የመሳሰሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን በፈፀሙ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ መሆኑን አብራርተዋል።
የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ በንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።

ንኡስ ግብረ ሀይሉ ወደ ተግባር ከገባ በኋላ ኑሮ ከማረጋጋት, ህጋዊ ስርአት እንዲጎለብት እና ገቢ እንዲያድግ ከማድረግ አኳያ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
ሆኖም ግን አሁን ባለው ሁኔታ በከተማዋ በአንዳንድ ምርቶች በተለይ የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪ እየታዩ በመሆኑ ንዑስ ግብረ-ሃይሉ ህገ-ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር የተናበበ እና የተቀናጀ ስራ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የንኡስ ግብረ ሀይሉ ሰብሳቢ አክለውም ህገ ወጥ የነዳጅ ፣ የዘይት፣ የኮንትሮባንድ እቃዎች ዝውውር ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግም አሳስበዋል።
የቅዳሜ እና የእሁድ ገበያዎች እና በከተማዋ የተገነቡ ትላልቅ የገበያ ማእከላት ላይ የሚካሄዱ ግብይቶች ከደላላ የጸዱና የታለመላቸውን አላማ በሚያሳካ መልኩ እየሰሩ መሆኑን የመቆጣጠር ስራ በትኩረት እንዲሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ያለደረሰኝ የሚነግዱ፣ ንግድ ፈቃድ ያላደሱ፣ ከዘርፍ ውጪ የሚነግዱና መሰልህገ-ወጥነቶች ላይ ጥብቅ ቁጥር እንዲደረግ ማሳሰባቸውንም ከአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።