በትግራይ ክልል ከአምስት ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶ ስልጠና አልፈው ማህበረሰቡን ተቀላቅለዋል – የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን

You are currently viewing በትግራይ ክልል ከአምስት ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶ ስልጠና አልፈው ማህበረሰቡን ተቀላቅለዋል – የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን

AMN – ታኀሣሥ 10/2017 ዓ.ም

በትግራይ ክልል 5 ሺህ 728 የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶ ስልጠና አልፈው ማህበረሰቡን መቀላቀላቸውን የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን አስታወቀ።

በኮሚሽኑ የፕሮግራም ዕቅድና ክትትል ዳይሬክተር ኮሎኔል በላይ አበበ፤ በትግራይ ክልል 75 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን በአራት ወራት ውስጥ በተሀድሶ ስልጠና ወደ ማኅበረሰቡ የመመለስ ስራ በተቀመጠው መርሃ ግብር እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በዚህ ሂደትም 5 ሺህ 728 የቀድሞ ታጣቂዎች በመቀሌና ዕዳጋ ሀሙስ ማዕከላት በማስገባት የተሀድሶ ስልጠናቸውን አጠናቀው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን አስታውቀዋል።

የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደተሀድሶ ስልጠና የማስገባት ስራ መቀጠሉን ጠቁመው፣ በእስከ አሁኑ ሂደትም በአጠቃላይ 6 ሺህ 625 የሚጠጉ የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች በተሀድሶ ስልጠና እንዲያልፉ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና የማሳለፍ ሂደት መቀጠሉን ገልጸው፣ አሁን ላይም በመቀሌና ዕዳጋ-ሀሙስ ማዕከላት 889 የቀድሞ ታጣቂዎች ስልጠናቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

በክልሉ ለቀድሞ ታጣቂዎቹ የሚሰጠው ስልጠና መደበኛ ህይወታቸውን በሚገባ መምራት በሚያስችል መንገድ መሆኑን አብራርተዋል።

በቀጣይም በትግራይ ክልል በዓድዋ ከተማ አካባቢ የሚገኘውን የአዲበራህ የስልጠና ማዕከል የዕድሳት ስራ በማጠናቀቅ የተሀድሶ ስልጠና የቅበላ አቅም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልል ደረጃም ሁለተኛው የተሀድሶ ስልጠና በአፋር ክልል 1 ሺህ 750 የአፋር ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ አብዓላ ተሀድሶ ስልጠና ማዕከል በማስገባት ስልጠና እየተሰጠ ስለመሆኑ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተደረሱ የሰላም ስምምነቶች መነሻነት ለቀድሞ ታጣቂዎች የሚሰጡ የተሀድሶ ስልጠናዎችም ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አንስተዋል።

All reactions:

108Sebel Assefa and 107 others

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review