
AMN-ጥር 7/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብ ሥርዓት መፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ።
በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብና ሥርዓተ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ላይ ትኩረቱን ያደረገ ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆይ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በመርህ ግብሩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ የተለያዩ ተቋማት አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፥ የኢትዮጵያን የምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በአገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ስርዓተ ምግብ ለመፍጠር ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመዋል።
ይህም የግብርና እና ጤና ሚኒስትሮች በጋራ የሚመሩት 15 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን የያዘ ስቲሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እንዲተገበር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የምግብና እና ስርዓተ-ምግብ ሽግግርን ለማረጋገጥ ብሎም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብ ሥርዓት ለመፍጠር የሚከናወኑ ቅንጅታዊ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሚኒስትሩ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፥ የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ እና የተመጣጠነ ምግብን ተደራሽ ለማድረግ የሰቆጣ ቃልኪዳንን መተግበርን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በህጻናት ላይ ሊከሰት የሚችለውን መቀንጨር ለመከላከልም የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ላይ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ሁሉንም ዘርፍ የሚነካ መሆኑን ጠቁመው ይህን ለመቋቋም በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና የስርዓተ-ምግብ ለውጥ ለማምጣት እያከናወነችው ያለው ስራ ለሌሎችም ምሳሌ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በተመድ የምግብና የእርሻ ድርጅት የምግብ ሥርዓት ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ካህሊድ ኤልታዊል ናቸው።
ኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብን ለማሻሻል ጥሩ ውጤት ማስመዝገቧንም ገልጸዋል።