
AMN-ኅዳር 5/2017 ዓ.ም
በከተማዋ በየትኛውም አካባቢ የሚካሄድ ግብይት በደረሰኝ ብቻ እንዲፈፀም የሚደረግ ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ዛሬ በመርካቶ ካሉ የነጋዴ ማህበር ተወካዮች ጋር በደረሰኝ ግብይት ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል ።
መድረኩን የመሩት የቢሮው ሀላፊ አቶ ቢንያም ምክሩ ፣ በመርካቶም ሆነ በከተማዋ የሚካሄዱ ግብይቶች በደረሰኝ ላይ ብቻ የተመሠረተ እንዲሆን ከተማ አስተዳደሩ በርካታ ስራዎችን አስቀድሞ መስራቱንና እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
አስመጪ ፣ አከፋፋይ ፣ አምራችና ቸርቻሪዎች ጋር ያሉ ችግሮችን በጥናት በመለየት እና መድረኮችን ፈጥሮ በመወያየት ወደ ህጋዊነት ለመግባት አስቻይ ስራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል።
ከህዳር 01 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአስመጪ፣ በአከፋፋይ ፣በአምራችና በቸርቻሪ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር እየተካሄደ መሆኑንም አመላክተዋል ።
በመሆኑም በከተማዋ በደረሰኝ ብቻ መገበያየት ላይ መንግስትም ሆነ ከተማ አስተዳደሩ ለድርድር የማያቀርበው ጉዳይ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል ።
በደረሰኝ መገበያየት የመንግስት እና የከተማ አስተዳደሩ ጥብቅ አቋም መሆኑን ያብራሩት አቶ ቢንያም በደረሰኝ ለመገበያየት የሚስተዋሉ ችግሮችን ህገወጥ ደላሎች ፣ አጭበርባሪዎችንና ደረሰኝ መስጠት የማይፈልጉ አምራች፣ አስመጪና አከፋፋይን ማጋለጥ ፣ ጥቆማ መስጠትና ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመቆም በጋራ ለለውጥ ልንሰራ ይገባል ብለዋል ።
በአሁኑ ወቅት አስመጪ፣ አከፋፋይ ፣ አምራችና ቸርቻሪ ነጋዴዎች ያለደረሰኝ መገበያየት የማይችሉ መሆኑን የገለፁት ሀላፊው ለዚህም በመርካቶ ለሚደረግ ቁጥጥር አዲስ ሰራተኞች በማደራጀት በ58 ብሎኮች በመመደብ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል።

ቸርቻሪ ነጋዴዎች ራሳቸውን ካለደረሰኝ ግብይት ሊጠብቁና በደረሰኝ ግብይት ሊፈፅሙ እንደሚገባም ተመላክቷል።
ከተማዋ ከምትሰበስበው ገቢ 63 በመቶ የሚሆነው በከተማዋ ለሚታዩ ሰው ተኮር ልማትና ሜጋ ፕሮጀክቶች እንደሚውል የተገለፀ ሲሆን ለዚህ ስኬት የንግዱ ማህበረሰብ በደረሰኝ በመግዛትና በመገበያየት ሚናውን ሊወጣና መብቱን ሊያስከብር እንደሚገባ አንስተዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ አከፋፋይና ቸርቻሪ ነጋዴዎች በንግድ ዘርፉ ከደረሰኝ ጋር በተያያዘ አሉ ያሏቸውን ችግሮች በማንሳት ውይይት የተደረገ ሲሆን በደረሰኝ ግብይት መፈፀም ላይ ከመግባባት መደረሱን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
All reactions:
7979