AMN – ታኀሣሥ 16/2017 ዓ.ም
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሴት ዲፕሎማቶች እና ሠራተኞች በአመራር ክህሎት፣ በተግባቦት እና ራስን በማብቃት እና መሠል የዲፕሎማሲ ክህሎቶች ዙሪያ ሥልጠና መስጠት ተጀምሯል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በሥልጠናው መክፈቻ ላይ በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሴቶችን የአመራር ድርሻ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴት ዲፕሎማቶችን የአመራር ድርሻ ለማሳደግ አጋዥ የሆኑ ስልቶችን በመንደፍ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አንስተዋል።
ሥልጠናው ራሳቸውን ከማብቃት አልፈው በዲፕሎማሲው በንቃት በመሳተፍ እና በመንቀሳቀስ አገራቸውን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ጽ/ቤት ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አዚዛ ገለታ በበኩላቸው፣ ሥልጠናው በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሴቶችን የአመራር ድርሻ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የተጀመረው ከፍተኛ ንቅናቄ መጀመሪያ ነው ብለዋል።
በቀጣይም በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የክህሎት እና የአመራር ጥበብን የሚያሳድጉ ሥልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።