AMN- ጥር 21/2017
ችግርና ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመለወጥ ካስቀመጥነው ጊዜ ቀድመን ብልፅግናን ማረጋገጥ እንችላለን ሲሉ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር እና የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ጌታሁን አብዲሳ አስገነዘቡ፡፡
ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ በሰጡት ማብራሪያ ብልፅግና በለውጡ ካካተታቸው ዋና ዋና ተግባራት ውስጥ አካታችነት ዋነኛው መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረው የፖለቲካ ምህዳር አንዱን የድርጅት አባል ሌላውን አጋር ብሎ ያስቀምጥ እንደነበር አስታውሰው ብልፅግና ግን ይህን አስወግዶ ሁሉንም በእኩልነት የሚያይ አካታች የሆነ አንኳር ለውጥ አስመዝግቧል ብለዋል፡፡
ፓርቲው ህዝብን እንደ ህዝብ በማክበር ዜጎችንም እኩል በማየት የፖለቲካና የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉንም አብራርተዋል ፡፡
አንዳንድ ክልሎች በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው ቀጥተኛ ተሳታፊና ተጠቃሚ አልነበሩም ያሉት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ክልሎቹ አናሳ ተብለው መሪዎቹን ሁሉ መምረጥ የማይችሉበት ስርዓት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
ዛሬ ላይ ግን በአራቱም አቅጣጫ ያሉ ዜጎች መሪዎቻቸውን በእኩልነት የሚመርጡበት የለውጥ ስርዓት ተገንብቷል ብለዋል ፡፡
ቀደም ሲል በነበረው ስርዓት የልዩነት ሀሳብ ሲነሳ የሚፈረጁበት ሁኔታ እንደነበረ እና አሁን ግን ማንም ሰው የመሰለውን አመለካከት በማንሳት በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገርና ችግሮችን የመፍታትና በትብብር አብሮ የመስራት ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ፡፡
የነበረውን የፖለቲካ ስሪት በመቀየር አሁን ላይ ተዓምራዊ ለውጥ መጥቷል ብለዋል ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ፡፡
ከዚህ ቀደም አሸናፊና መሪ ፓርቲ የሚባለው ከላይ እስከ ታች ወጥ የሆነና በአንድ ፓርቲ የሚመራበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ዛሬ ማንኛውም ተፎካካሪ ፓርቲ ሀሳቡን በነፃነት የሚያራምድበትና ከጫካ ወደ ሜዳ ከልዩነት ወደ አንድነት የመጣበት የፖለቲካ ምህዳር መፈጠሩንም ጠቁመዋል ፡፡
ብልፅግናን የማረጋገጥ ተግባር የሁሉም አካላት ሚና መሆኑን ያስታወቁት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
ችግርና ፈተናዎችን ወደ እድል በመለወጥ ካስቀመጥነው ጊዜ ቀድመን ብልፅግናን ማረጋገጥ እንችላለንም ብለዋል፡፡
በሽመልስ ታደሰ