ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አባልነት ልትወዳደር ነው

AMN – ታኅሣሥ – 10/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት የእ.አ.አ 2025 እስከ 2027 የቆይታ ዘመን አባል ለመሆን ዕጩ መሆኗን ይፋ አደረገች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ የአፍሪካ አምባሳደሮች ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል ለመሆን እንደምትወዳደር አብስረዋል።

ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ አባልነት ለምታደርገው ውድድር የሕብረቱ አባል ሀገራት አምባሳደሮች ለአፍሪካ የዋለችውን ታሪካዊ ሚና ከግንዛቤ በማስገባት በውሳኔ ሂደቱ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በቀጣናው እና በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ለረጅም ዘመናት በቁርጠኝነት ስትሰራ መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ አፍሪካ ከቅኝ አገዛዝ እንድትወጣ የተጫወተችውን ወሳኝ ሚና እንዲሁም የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች አገር መሆኗን ጠቅሰው፤ በአህጉራዊ አጀንዳዎች ላይ አበክራ ስትሰራ መቆየቷን አመልክተዋል።

የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ትብብርን በማጎልበት እና የአፍሪካን የጋራ ድምጽ በማሰማት የአጀንዳ 2063 ግቦች እንዲሳኩ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review