እንደ ሀገር ሸማች ሳይሆን አምራች መሆን አለብን- ኤፍሬም ግዛው (ዶ/ር)

You are currently viewing እንደ ሀገር ሸማች ሳይሆን አምራች መሆን አለብን- ኤፍሬም ግዛው (ዶ/ር)

AMN – ሚያዚያ 2/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከሸማችነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር የሚያስችል የኢንዱስትሪ መር ተግባራት ላይ እንደምትገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንደስትሪ ልማት ቢሮ በቢሮ ሃላፊ ደረጃ የፋሲሊቲና የካይዘን ትግበራ ዘርፍ ሃላፊ ኤፍሬም ግዛው (ዶ/ር) ገልፀዋል።

ኤፍሬም ግዛው (ዶ/ር) ይህን ያሉት “የፋይናንስ አቅርቦት ለኢንዱስትሪ ምርታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ ስኬት ባንክ እያካሄደ ባለው የፓናል ውይይት ላይ ነው።

የአምራች ዘርፉ አሁን ላይ ጥራት ያለው ምርት እያመረተ በመሆኑ ሸማቹ የሀገር ውስጥ ምርትን መጠቀም ላይ ያለው ባህል እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

የአምራች ዘርፉን ውጤታማነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በርካታ ፓሊሲዎችን በመቅረፅ እያገዘ መሆኑንም ተናግረዋል።

የፋይናንስ እና የኢንዱስትሪ ዘርፎችን ነጣጥሎ ማየት አይቻልም ያሉት የስኬት ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዳምጠው አለማየሁ፣ ባንኮች እና አምራች ዘርፉ አንዱ ያለ አንዱ ማደግ ስለማይችሉ በትብብር መስራት ላይ ትኩረት ማድረግ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የአምራች ዘርፉን ለመደገፉ ስኬት ባንክ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቅሰዋል።

በንጉሱ በቃሉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review