እንጆሪ እና ሳፍሮን በማምረት ለውጪ ገበያ የሚያቀርብ ኩባንያ ወደ ስራ ሊገባ ነው

You are currently viewing እንጆሪ እና ሳፍሮን በማምረት ለውጪ ገበያ የሚያቀርብ ኩባንያ ወደ ስራ ሊገባ ነው

AMN – መጋቢት 2/2017 ዓ.ም

በዘመናዊ መንገድ እንጆሪ እና ሳፍሮን በማምረት ለውጪ ገበያ የሚያቀርብ ኩባንያ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ስራ ሊገባ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በ2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ኢንቨስትመንት በዘመናዊ መንገድ እንጆሪ እና ለመድሃኒት ግብዓት የሚውል ሳፍሮን የተሰኘ አበባ በማምረት ለውጪ ገበያ የሚያቀርብ አፍሪካን ፋርሚንግ ኢንዱስትሪስ የተሰኘ ኩባንያ ነው ወደ ስራ እንደሚገባ የተመላከተው፡፡

ኩባንያው ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነትም ተፈራርሟል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) እና የአፍሪካን ፋርሚንግ ኢንዱስትሪስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ናሱር ማሃማት ተፈራርመዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ኩባንያው ይዞት የመጣው ፕሮፖዛል በኮርፖሬሽኑ የስራ ሂደት ውስጥ አዲስ መሆኑን ጠቅሰው ለውጤታማነቱ ተገቢው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የአፍሪካን ፋርሚንግ ኢንዱስትሪስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ናሱር ማሃማት በበኩላቸው እንደገለጹት፣ ኩባንያው ዘመናዊ ቴክኖሎጅን ተጠቅሞ በቨርቲካል ፋርሚንግ በማምረት ወደ ውጭ እንደሚልክና በዚህም ኢትዮጵያን ግንባር ቀደም የእንጆሪ እና ሳፍሮን ላኪ ሃገር ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

አፍሪካን ፋርሚንግ ኢንዱስትሪስ ኩባንያ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ 5000 ካሬ ሜትር የለማ መሬት እና 3000 ካሬ ሜትር ሼድ ተረክቦ ወደ ስራ የሚገባ ሲሆን ለበርካታ ዜጎች የስራ እድልን እና ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የቴክኖሎጂ ሽግግር ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review