ከህዳሴ ግድብ በቀን ከ14 ሺህ ቶን በላይ የአሳ ምርት እየተገኘ ነው- ግብርና ሚኒስቴር

You are currently viewing ከህዳሴ ግድብ በቀን ከ14 ሺህ ቶን በላይ የአሳ ምርት እየተገኘ ነው- ግብርና ሚኒስቴር

AMN – መጋቢት 17/2017

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቀን ከ14 ሺህ ቶን በላይ የአሳ ምርት የሚገኝበት አቅም መፈጠሩን በግብርና ሚኒስቴር አሳ ሀብት ልማት ዴስክ ሃላፊ ፋሲል ዳዊት (ዶ/ር) ገለጹ።

በግብርና ሚኒስቴር አሳ ሀብት ልማት ዴስክ ሃላፊ ፋሲል ዳዊት (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ እምቅ የአሳ ሀብት ቢኖራትም በተለያዩ ተግዳሮቶች ምክንያት በዘርፉ ተጠቃሚ ሳትሆን ቆይታለች ብለዋል፡፡

በሀገር ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአሳ ልማት ዘርፍ ማነቆ የሆኑ ተግዳሮቶችን በመፍታት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በዚህም በአሳ ምርታማነት ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን አንስተው፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውስጥ የአሳ ሀብት ልማት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በግድቡ በስፋት ተፈላጊ የሆኑ የአሳ ዝርያዎች እየተመረቱ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም በቀን ከ14ሺህ 500 ቶን በላይ የአሳ ምርት የሚገኝበት አቅም መፈጠሩን አብራርተዋል።

በህዳሴ ግድብ ውስጥ የተለያዩ የአሳ ዝርያዎች መኖራቸውን የገለጹት ዶክተር ፋሲል የሚመረተው አሳ ተፈላጊነት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘርፉ ካለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባለፈ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በቀጣይ የአሳ ምርትን የበለጠ ለማሳደግ የአሳ ጫጩቶችን ማሰራጨት እና አሳ በሌለባቸው የውሀ አካላት ላይ አሳ የሚመረትባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review