
AMN- ህዳር 9/2017 ዓ.ም
ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢንቨትመንት፣ የንግድ ልውውጥና ዲጂታል የግብይት ሥርዓት መደገፍና ማጠናከር እንደምትፈልግ በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ካንግ ጁንግ ተናገሩ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፥ በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደርን በቢሯቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይቱም፥ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከር፣ በኢንቨትመንትና በንግድ ልውውጥ ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ መክረዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የኢትዮጵያና የኮሪያ ሪፐብሊክ ግንኙነት ታረካዊ ነው ብለዋል።
አክለውም፥ በኮሪያ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ወታደሮች የኮሪያን ህዝብ በመወገን ተዋግተው የደም ዋጋ የከፈሉ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ የቡናና የቅባት እህል ወጪ ምርቶችን ወደ ኮሪያ ሪፐብሊክ ገበያ እንደምትልክ ገልጸው፥ ኢትዮጵያ ከኮሪያ ሪፐብሊክ ጋር ያላትን የኢንቨትመንት አማራጮችንና ዕድሎች ለአምባሳደሩ ገልጸዋል።
በመሆኑም የሀገሪቱ ባለሀብቶች ያሉትን ምቹ ሁኔታዎችን ተጠቅመው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የወሰደችው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ፈጣን እድገት ማስመዝገቡን የገለጹት ሚኒስትሩ የኮሪያ ሪፐብሊክ በዲጂታል ንግድና ግብይት ልምድ ያላት ሀገር በመሆኗ በኢኮሜርስና ዲጂታል ዘርፍ አቅም ግንባታና የልምድ ልውውጥ ድጋፍ እንዲታደርግ ጠይቀዋል፡፡
አምባሳደሩ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ካንግ ጁንግ፥ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢንቨትመንት፣ የንግድ ልውውጥና ዲጂታል የግብይት ሥርዓት መደገፍና ማጠናከር እንደምትፈልግ መናገራቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።