AMN – የካቲት 20/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበበ ከተማ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ የሕዝብን እና የመንግሥትን ውስን ሀብት በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል የመረጃ አስተዳደር ቴክኖሎጂ ስራ አስጀመረ፡፡
ቢሮው የመንግሥት የመኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ቤቶች እና የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በኦንላይን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የከተማ ቤቶች የመረጃ አስተዳደር ሲስተም በአቃቂ ቃሊቲ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስጀምሯል።
ይህ የከተማ ቤቶች የመረጃ አስተዳደር ሲስተም፣ የሕዝብን እና የመንግሥትን ውስን ሀብቶች በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ቅድስት ወ/ጊዮርጊስ ገልጸዋል።
የከተማ ቤቶች የመረጃ አስተዳደር ሲስተሙ የትኛውም ሰው ከፈለገበት ቦታ ሆኖ አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል ነው ብለዋል ኃላፊዋ።
ሲስተሙ፣ በየክፍለ ከተማው ያለውን የመንግሥት የመኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ቤቶች እና የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ማስተዳደር፣ የቤት መረጃ ምዝገባ ማካሄድ፤ የቤት ፈላጊዎች ምዝገባ አስተዳደር ማድረግ፤ የአከራይ ተከራይ የውል ምዝገባ መፈጸም እና ሌሎችም ተመሳሳይ አገልግሎቶችን በኦንላይን ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነም ገልጸዋል።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አዲሱ ሻንቆ (ዶ/ር) ውጤታማነት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያለ ቴክኖሎጂ አይታሰብም፣ በመሆኑም ቤትን በዲጂታል ቴክኖሎጂ መመዝገብ እና አገልግሎቱን መስጠት ግዴታ ነው ብለዋል።
በሕገወጥ ቤት መቀበል እና መስጠት ለማስቀረት እና ቅሬታን ለመቅረፍ መፍትሔ ይዞ የመጣ ቴክኖሎጂ እንደሆነም ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልጸዋል።
የከተማ ቤቶች የመረጃ አስተዳደር ሲስተም በቤቶች አስተዳደር በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይስተዋል የነበረውን ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ለመከላከልና በዘላቂነት መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል እና ዘመናዊ የቤቶች መረጃ ስርዓትን ተግባራዊ የሚያደርግ መሆኑን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የቤቶች አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ ኃ/ማርያም አበራ ተናግረዋል።
በዳንኤል መላኩ